Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
አቃቂ ቃሊቲ ለሚገኘው ሴቶች ማረፍያ እና ልማት ማኅበር 1.5 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ ድጋፍ ተደረገ
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጳጉሜ 4 “የሕብር ቀን” ምክንያት በማድረግ በአቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ ለማገኘው የሴቶች ማረፍያ እና ልማት ማኅበር ማዕድ አጋርቷል።
በዕለቱ የተቋሙ ከፍተኛ አመራሮች በማህበሩ በመገኘት የ2 መቶ ሺ ብር ገንዘብ እንዲሁም የቴምርና የንህጽና መጠበቅያ ፓድ ድጋፉን አበርክተዋል። በመርሐግብሩ ላይ በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የክብርት ሚኒስትር አማካሪ ክቡር አቶ ጌታቸው በዳኔ ባስተላለፉት መልዕክት፥ በብሔራዊ ደረጃ የምናከብረው “የሕብር ቀን” ዓላማው እርስ በእርስ የምንደጋገፍበት፣ አብሮነታችንና ማህበራዊ ትስስራችንን የበለጠ የምናጠናክርበትና የኢትዮጵያዊነት እውነተኛ ዕሴትን በተግባር የምናሳይበት መሆኑን ገልፀዋል።
አክለውም የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ለስርዓተ ጾታ እኩልነት መረጋገጥ እና ለማኅበራዊ ጥበቃ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል ብለዋል። የሴቶችን መብት ለማስጠበቅ ከሚደረገው ጥረት ጎን ለጎን በተለያየ ምክንያት ለጥቃትና ለችግር ለተጋለጡ ሴቶች የማህበራዊና ስነልቦናዊ ድጋፍ ለመስጠትና በዘላቂነት መልሶ ለማቋቋም የሚያግዙ ተግባራትን ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በዛሬው ዕለትም የህብር ቀንን ምክንያት በማድረግ ለጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች ማረፍያ እና ልማት ማኅበር 1.5 ሚሊዮን ብር በዓይነትና በገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን አስታውቀዋል።
የሴቶች ማረፍያ እና ልማት ማኅበር ዋና ስራ አስኪያጅ እና መስራች ወ/ሮ ማርያ ሙኒር በተደረገው ድጋፍ መደሰታቸውን ገልፀው ለተረገው ድጋፍ በተጠቃሚ ወገኖች ስም ምስጋና አቅርበዋል።
