“ለሀገር ክብርና ለዜጎች ጥቅም የሚጠበቅብንን ኃላፊነት እንወጣለን” – የተቋሙ አመራርና ሠራተኞች

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አመራሮችና ሠራተኞች 19ኛውን ብሔራዊ የሠንደቅ ዓላማ ቀን በተለያዩ መርሐግብሮች አከበሩ።
በዓሉ ዘንድሮ ለ19ኛ ጊዜ “ሠንደቅ ዓላማችን ለብሔራዊ መግባባትና ለአንድነታችን” በሚል መሪ ቃል በሀገር አቀፍ ደረጃ በድምቀት እየተከበረ ይገኛል።በዓሉን አስመልክቶ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ያስተላለፉት በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የክብርት ሚኒስትር አማካሪ ክቡር አቶ ጌታቸው በዳኔ እንደገለጹት፤ ሠንደቅ ዓላማ የአንድ ሀገር መንግሥትና ሕዝብ ሉዓላዊነት፣ የፖለቲካ ሥልጣን፣ ነፃነት፣ ዕድገትና ማሕበረሰባዊ ትስስር መፍጠሪያ ታላቅ የብሔራዊ ኩራት አርማ ነው። ጀግኖች አያቶቻችን ወራሪዎችን በማሸነፍ ለአዲሱ ትውልድ ያስረከቡት ሠንደቅ ዓላማ የመላው ጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ምልክት መሆኑን ገልፀዋል።
የሠንደቅ ዓላማችንን ክብርና ተገቢውን ከፍታ አስጠብቆ ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ ሀገራዊ ሉዓላዊነትን፣ የግዛት አንድነትንና ሕብረ ብሔራዊ ወንድማማችነትን ማጽናት ይገባል ብለዋል።
ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ለሠንደቅ ዓላማው የሚገባውን ክብር የመስጠትና የማክበር ግዴታ እንዳለበት ክቡር አቶ ጌታቸው በዳኔ አሳስበዋል።
የተቋሙ አመራርና ሠራተኞች ለሀገር ክብርና ለዜጎች ጥቅም የሚጠበቅብንን ኃላፊነት እንወጣለን ሲሉ በሠንደቅ ዓላማችን ፊት ቃለመሐላ ፈፅመዋል።
Please follow and like us: