Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
በውጤታማ አካታችነት ማህበራዊ ፍትህ የሰፈነባትና የነገይቱን የበለጸገች ኢትዮጵያ ለመገንባት የጋራ ርብርቡ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀረበ
(አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 28/2019 ዓ.ም) በውጤታማ አካታችነት፣ ማህበራዊ ፍትህ የሰፈነባትና የበለጸገች ኢትዮጵያን እንገነባለን!” በሚል መሪ ቃል የሚካሄደውን የጋራ ጉባኤ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ሸዊት ሻንካ በይፋ አስጀምረዋል።

በመክፈቻ ስነ-ስርዓቱ ላይ ክብርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ ባስተላለፉት መልዕክት፥ መደመር ፍልስፍና ሀገራዊ አንድነታችንን ከማጠናከር ባለፈ፣ ማህበራዊ ፍትህን እውን ለማድረግ፣ የዜጎችን እኩል ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እና ድህነትን በዘላቂነት ለመሻገር ማዕከል መሆኑን ገልፀዋል። ሴክተሩ በዚህ ሰፊ ሀገራዊ ማዕቀፍ ውስጥ ያለው ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው የሚወሰኑ ማናቸውም ውሳኔዎች ማህበራዊ ፍትህ የሰፈነባትና ለነገይቱ የበለጸገች ኢትዮጵያ መሠረት የሚጥሉ መሆናቸውን አንስተዋል።

ስለሆነም በሴክተሩ የሚወሰዱ ስትራቴጂዎች የሰው ልጅን ሁለንተናዊ ጉዞ ማዕከል ያደረጉና የሁሉንም ዜጎች እኩል ተሳትፎና የፆታ እኩልነት የሚያረጋግጡ፣ አካታችነትንና ጠንካራ የፍትህ ስርዓት በመገንባት የማህበራዊ ግቦችን ለማሳካት ከፍተኛ ሚና አላቸው ብለዋል። ሀገራችን የኢትዮጵያ ስልጣኔ እውን ለማድረግ የሴቶችን፣ አቅመ-ደካሞችን፣ ህፃናትን እና አካል ጉዳተኞችን ጨምሮ ሁሉንም ህዝባችን በአጠቃላይ የልማቱ ተጠቃሚና ባለቤት ማድረግ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ሀገራችን ኢትዮጵያ በቀጠናው እና በአፍሪካ ደረጃ ያላትን የመሪነት ሚና አጠናክሮ ለማስቀጠል፤ በዘርፉ የተቀመጡትን የአህጉራዊ መሪነት ግቦች ለማሳካት በልዩ ትኩረት እና ቅንጅት መስራት ይገባል ብለዋል፡፡በውጤታማ አካታችነት ማህበራዊ ፍትህ የሰፈነባትና የነገይቱን የበለጸገች ኢትዮጵያ ለመገንባት የገባነው ቃል እንዲሳካ የጋራ ርብርቡ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።
