Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
ከተለያዩ የፌዴራል መንግስት መስሪያቤቶች የተመለመሉና በህፃናት አያያዝ እና እንክብካቤ የ6 ወራት ስልጠናን ላጠናቀቁ የስራ ቦታ የህጻናት ማቆያና መንከባከቢያ ማዕከላት ተንከባካቢዎች የምርቃት ፕሮግራም ተካሄደ፡፡
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፓርትነርሺፕ ፎር ቼንጅ እና ከዝግጁ የስልጠና እና ማማከር ተቋም ጋር በመተባበር ላለፉት ስድስት ወራት ያሰለጠናቸውን የህጻናት ተንከባካቢዎች አስመረቀ፡፡
የስልጠና ዕድሉ ተጠቃሚ የሆኑት ከተለያዩ የፌዴራል መንግስት መስሪያ ቤቶች የተመለመሉ 73 የመንግስት የስራ ቦታ የህጻናት ማቆያን መንከባከቢያ ማዕከላት የህጻናት ተንከባካቢዎች ሲሆኑ እስካሁን በ9 ዙር በተሰጠ ስልጠና ከ530 በላይ የሚሆኑ ተንከባካቢዎችን አሰልጥኖ ማስመረቅ ተችሏል፡፡

በምርቃት ስነስርዓቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የአካቶ ትግበራ ክትትል፣ ድጋፍና ቁጥጥር መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ከተማ ለገሰ ሚኒስቴር መስሪያቤቱ የህጻናት ማቆያና መንከባከቢያ ማዕከላትን በተለያዩ ዓይነቶች በማስፋፋት የሚያስችል የአሰራር ስርዓቶችን በመዘርጋት ሴቶችና ህጻናትን ተጠቃሚ ለማድረግ ተግባራዊ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በተለይም ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት በተሰሩ የስርዓት ዝርጋታ እንዲሁም ጠንካራ የክትትልና ድጋፍ ስራዎች በሃገር አቀፍ ደረጃ ከ1200 በላይ የመንግስት ስራ ቦታ የህጻናት ማቆያና መንከባከቢያዎችን በማደራጀት የነገ ሃገር ተረካቢ ዜጎች ጤናማ አካላዊ፣ አዕምሮአዊ እና ማህበራዊ እድገት እንዲኖራቸውና ጠንካራ የስብዕና መሰረት እንዲኖራቸው ከማድረግ አንጻር ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያለው መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ በተለይም በስራ ቦታዎች ላይ የሚቋቋሙ የህጻናት ማቆያና መንከባከቢያ ማዕከላት ለሴት ሰራተኞች ምቹ የስራ ሁኔታን በመፍጠር ሴት ሰራተኞች ሙሉ አቅማቸውን ተጠቅመው አምራች ሃይል እና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ከማድረግ አንጻር ቁልፍ አስተዋጽዖ እያበረከተ ይገኛል ብለዋል፡፡

በመደበኛ ስራ ላየ ካሉ ሴት ሰራተኞች ባለፈ መደበኛ ባልሆነ ስራ ላይ የተሰማሩ ሴቶች ከወሊድ በኋላ በሚኖር ህጻናትን የመንከባከብ ሃላፊነት ምክንያት በቤት ውስጥ በመዋል ጥገኛ እንዳይሆኑና በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ መስኮች የእኩል እድል ተሳታፊ እና ተጠቃሚ መሆን እንዲችሉ እድል የፈጠረ መሆኑንና ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠር መቻሉን ጠቁመዋል፡፡ አገልግሎቱን በሃገር አቀፍ ደረጃ የማስፋፋትና የማጠናከር ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በማሳወቅ የዚህ ዙር ሰልጣኝ ተመራቂዎች በቀጣይ በተመደቡበት የስራ መስክ በስልጠና ያገኙትን ዕውቀትና ክህሎት ከሙያዊ ስነምግባር ጋር በማስተሳሰርና ወደ ተግባር በመቀየር ለህጻናት ዕድገትና ደህንነት የበኩላቸውን አስተዋጽዖ እንዲያበረክቱ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በመጨረሻም ለዚህ ስልጠና መሳካት ጉልህ አስተዋጽዖ ለነበራቸው የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የስራ ክፍል ሃላፊዎችና ባለሙያዎች፣ የዝግጁ የማማከርና ስልጠና ተቋም አመራሮችና አሰልጣኞች፣ የቴክኒክ እና የገንዘብ ድጋፍ ያደረጉትን ፓርትነርሺፕ ፎር ቼንጅ እና የኢትዮጵያ ሴቶች ጤና ማህበርን አመስግነዋል፡፡
