በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ በህፃናት ተንከባካቢ ሞግዚቶች ዙሪያ ሲሰጥ የነበረው የመምህራን የአሰልጣኞች ስልጠና ተጠናቀቀ

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴርና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በህፃናት መንከባከቢያ ማዕከላት፣ በህፃናት ማሳደጊያዎችና በሌሎች ለህፃናት አገልግሎት በሚሰጡ ተቋማት ውስጥ የሚያገለግሉ ብቁ ባለሙያዎችን ለማፍራት ያዘጋጀውን ስልጠና በስኬት አጠናቋል።

‎በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በቴክኒክና ሙያ ተቋማት ደረጃ (ከደረጃ 2 – 4) በአጭርና በረጅም ጊዜ ስልጠና ለመስጠት የሚያስችል የህፃናት ሁለንተናዊ ዕድገት፣ ጤና፣ ማነቃቃት፣ ጥበቃና መብትን ያካተተ ካሪኩለምና የማሰልጠኛ ማኑዋል ተዘጋጅቷል። የተዘጋጀውን ካሪኩለም ወደታች በማውረድ ተግባራዊ ለማድረግ ከሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ለተውጣጡ 59 ብቁ የቴክኒክና ሙያ መምህራን ስልጠናው ተሰጥቷል። ሰልጣኞቹ የወሰዱትን የንድፈ-ሃሳብ ስልጠና ከተግባር ጋር ለማስተሳሰር በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሚገኙ 6 የህፃናት መንከባከቢያ ማዕከላትን በአካል ተገኝተው ጎብኝተዋል።

‎በመርሐግብሩ ላይ የህፃናት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ ጥሩማር አባተ፤ ህፃናት በስነምግባር ታንጸው፣ በአካልና በአእምሮ ዳብረው ሀገር ወዳድ ዜጋ ሆነው እንዲያድጉ በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል ወሳኝ መሆኑን ገልጸው፣ ተመራቂ መምህራን ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት እንዲሰጥ የበኩላቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል። ‎በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ አቶ አዝማራው በቀጣይ ስለሚከናወኑ ተግባራት አቅጣጫ የሰጡ ሲሆን፣ በመጨረሻም ለሰልጣኞችና ለአሰልጣኝ መምህራን የእውቅናና የምስጋና ሰርተፊኬት ተበርክቷል።

Please follow and like us: