የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አመራሮችና ሰራተኞች በአዲስ አበባ በዘርፉ የተከናወኑ ሰው ተኮር የልማት ስራዎችን ጎበኙ

(አዲስ አበባ፣ ህዳር 14/2019 ዓ.ም) የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አመራሮችና ሰራተኞች በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሴቶች፣ በህፃናትና በማህበራዊ ዘርፍ የተከናወኑ የተቀናጁ የልማት ፕሮጀክቶችን በዛሬው ዕለት ተዟዙረው ጎብኝተዋል።

የጉብኝቱ ዋና ዓላማ የመንግሥትን ሰው ተኮርና አካታች የልማት ዕሳቤዎች በተግባር በመመልከት የሰራተኞችን የስራ ተነሳሽነት ማሳደግ ነው። በጉብኝቱ በጉለሌ የተገነባው የተቀናጀ የልማት መንደር ከ500 በላይ የቀድሞ እንጨት ተሸካሚ ሴቶች በእንጀራ አቅርቦትና በከተማ ግብርና ተሰማርተው የገበያ ትስስር የተፈጠረላቸው ሲሆን፣ የመኖሪያ ህንፃዎች፣ የህፃናት ማቆያና የምገባ ማዕከላት ህይወታቸውን እየቀየሩ መሆኑ ተመልክቷል።

በዕለቱ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ የሚገኝ የሕፃናት እንክብካቤ ማዕከል አገልግሎት አሰጣጥ ተጎብኝቷል። በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የብርሃን ተስፋ የአይነስውራን አዳሪ ትምህርት ቤት፣ የነገዋ የሴቶች የክህሎት ማበልፀጊያ ልህቀት ማዕከል እና በግሉ ዘርፍ የተገነባው የሰንሻይን ፊላንትሮፒ የአረጋውያን መጦሪያ ማዕከል ተጎብኝተዋል።

 

በጉብኝቱ ማጠቃለያም መንግሥት፣ የግሉ ዘርፍና ማህበረሰቡ በየአካባቢው በቅንጅት የጀመሯቸውን መሰል ሰው ተኮር ፕሮጀክቶች በፍጥነት፣ በጥራትና በፈጠራ በማስፋት የዜጎችን ተጠቃሚነት ይበልጥ ማላቅ እንደሚገባ ተገልጿል።

Please follow and like us: