Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሴቶችና እናቶችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያከናውናኑ ተግባራት ስኬታማ እንዲሆኑ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እገዛና ድጋፍ እንደሚያደርግ ተገለጸ
(አዲስ አበባ፣ ግንቦት 10/ 2015 ዓ.ም) የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አንዴማማ ሀገር በቀል ግብረ ሰናይ ድርጅት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሴቶችና እናቶችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ለሚያከናውናቸው ተግባራት ስኬታማነት እገዛና ድጋፍ እንደሚያደርግ የሚኒስትር ጽ/ቤት ኃላፊዋ ወ/ሮ እታገኝ አሰፋ ገለጹ፡፡

ይህ የተገለጸው የሚኒስትር ጽ/ቤት ኃላፊዋ ወ/ሮ እታገኝ አሰፋ አንዴማማ ማኑፋክቸሪንግ ኃ/የተ/አ/ማ የተባለው ሀገር በቀል ግብረ ሰናይ ድርጅት አለም አቀፍ የእናቶች ቀንን ምክንያት በማድረግ የእናቶችን ውለታና ስኬት ለመዘከር እና 2ኛ ዓመት የምስረታ ክብረ በዓሉን “Gratitude for Impact, Innovation & Inspiration” በሚል መሪ ቃል በዛሬው እለት በኢንተርኮንቲኔታል ሆቴል ለማክበር ባዘጋጀው ልዩ ፕሮግራም ተገኝተው መልዕክት ባስተላልፉበት ወቅት ነው፡፡
በዚሁ ጊዜም ኃላፊዋ እንደተናገሩት፤ “እናትነት በዘመን የማይጠወልግ፣ በጊዜ የማያረጅ፣ በወረት የማይደበዝዝ የጊዜን ድንበር ተሻግሮ የሚዘልቅ የሰውነት ልክ ማሳያ ነው፡፡ እናት ማለት ለብዙዎቻችን ወላጅ ብቻ አይደለችም፤ “የደግነት፣ የሩህሩነት፣ የብርታትና የጥንካሬ ተምሳሌት ጭምር ነች፡፡” ብለዋል፡፡
ሴቶችና እናቶች ባለውለታ ቢሆኑም የድካማቸውን ያህል ተጠቃሚ አይደሉም ያሉት ኃላፊዋ፤ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የመንግስት አካላትን ተግባርና ኃላፊነት ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 1262/2014 መሰረት የሴቶችን፣ የእናቶችን፣ የአረጋውያንንና ሌሎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት በመስጠት ተሳትፎና ተጠቃሚነታቸውን እንዲሁም ማህበራዊ ደህንነታቸውን ለማረጋገጥ ከተለያዩ ባለድርሻና አጋር አካላት ጋር በመተባበር በርካታ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን አንስተዋል፡፡

የእናት ፍቅር መንፈስ ወይም The Sprit of Mama’s Love የተሰኘ ፕሮጀክት በመቅረጽ ወደ ስራ የገባው አንዴማማ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ሴቶችና እናቶች የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማድረግ የሚያስችሉ በርካታ ተግባራትን እያከናወኑ መሆኑንና በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ውስጥ የሚሰሩ 30 የጽዳት ሰራተኞችም የፕሮክቱ ተጠቃሚ መሆን መቻላቸውን ገልጸዋል፡፡
ድርጅቱ ትልቅ ሃሳብ ትልቅ ራዕይ ሰንቆ እየተንቀሳቀሰ በመሆኑ ሊመሰገን ይገባል ብለዋል፡፡
በቀጣይም ድርጅቱ ለሚያከናውናቸው ተግባራት ስኬታማነት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር አስፈላጊውን እገዛና ድጋፍ እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡

የድርጅቱ ዋና ሰብሳቢ አስኪያጅ አቶ አንዷለም ኃይለጊዮርጊስ በበኩላቸው ቆሻሻን በማቃጠልና በመጣል የሚፈጠረውን የአካባቢና የአየር ብክለትና የአፈር ለምነትን ችግር ከመቀነስ ባሻገር አካባቢን ለዓይን የሚስብ ጽዱና ውብ ለስራም፣ ለመኖሪያና ለመዝናኛም ጭምር ምቹ እንዲሆን እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
ውጥኑ እንዲሳካም ሁሉም በቅንነት፣ በትብብርና በቅንጅት መንፈስ እንዲሰራ የተጀመረውም ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አቶ አንዷለም አደራ ብለዋል፡፡
