ወላጆቻውን በተለያዩ ምክንያቶች ያጡና በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን በጋራ ለመደገፍ የሚያስችል የፕሮጀክት መግባቢያ ስምምነት ፊርማ ተካሄደ

(አዲስ አበባ፣ ግንቦት 18/2015 ዓ.ም) “በጎ ፈቃድ ለሀገር ግንባታ” በሚል መሪ ቃል ወላጆቻውን በተለያዩ ምክንያቶች ያጡና በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ለመደገፍ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን የአምስት አመት የፕሮጀክት መግባቢያ ስምምነት ፊርማ ተካሄደ።

 

የፕሮጀክት ስምምነቱ የተካሄደው በኢፌ.ዴ.ሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ በኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ባለስልጣን እና አሊያንስ ኬር ፎር ናው /Alliance Care for Now/ በተባለ አጋር ድርጅት መካከል ነው።

በመግባቢያ ሰነዱ ላይ የኢፌ.ዴ.ሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ፣ የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ባለስልጣን ክቡር አቶ ጂማ ዲልቦ እንዲሁም የአሊያንስ ኬር ፎር ናው /ACN/ መስራችና ዋና ስራ አስኪያጅ ወ/ሮ ናኦሚ ሀይሌ ተገኝተው ፊርማቸውን አኑረዋል።

 

የፕሮጀክት ስምምነቱ ለአምስት አመት የሚቆይና በሁሉም ክልሎች የሚተገበር ሲሆን ወደ ትግበራ ሲሸጋገርም አምስት ሚሊዮን ያህል ዜጎችን በተለያዩ  ፕሮግራሞች ተጠቃሚ ለማድረግ ግብ መጣሉ ተገልጿል።

ፕሮጀክቱን ለማስፈጸም እንዲረዳም በቀጣዮቹ አምስት አመታት አምስት ሚሊዮን ሀገር በቀል በጎ ፈቃደኞችን ለማሳተፍ ዕቅድ መያዙ ተጠቁሟል።

 

በፕሮግራሙ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የኢፌ.ዴ.ሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ እንደተናገሩት፤ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አለም አቀፍ የልማት አጋራትን በማሳተፍ፣ የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን በማጠናከር እንዲሁም የሀገር ውስጥ ሰፊ አቅምን በመጠቀም በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮች ምክንያት የተጎዱ እና በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ለመደገፍ የሚያስችሉ በርካታ ስራዎችን በቅንጅት እየሰራ ይገኛል።

 

በየጊዜው በተካሄዱ የማህበረሰብ ንቅናቄዎች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በግለሰብ፣ በማህበረሰብና በተቋም ደረጃ ባህል ተጠናክሮ መቀጠሉን የተናገሩት ሚኒስትሯ፤ ባለፉት አመታት በዘርፉ በርካታ ውጤታማ ስራዎች መሰራታቸውን ገልጸዋል።

 

ሀገራችን ኢትዮጵያ መደጋገፍንና መተሳሰብን መሰረት ያደረጉ በርካታ ማህበራዊ እሴቶች ያሏት እንደመሆኑ መጠን እነኚህን የበለጠ ማጎልበት፣ በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል፣ ቀጣይነት እንዲኖረው በስርዓት መደገፍ እንዲሁም ተባብረንና ተቀናጅተን መስራት ከተቻለ የህብረተሰቡን ችግሮች ከመቅረፍ ባሻገር ለሀገር ግንባታ ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከት ይቻላልም ብለዋል።

 

ወላጆቻውን በተለያዩ ምክንያቶች ያጡና በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን በተለያዩ አማራጮች መደገፍ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ትኩረት ሰጥቶ ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል አንዱና ዋነኛው በመሆኑ በቀጣይ የፕሮጀክት ስምምነቱን በክረምትና በበጋ በመደበኛነት ከሚካሄደውና ከወሰን ተሻጋሪ የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሃ ግብሮች እንዲሁም ከሌሎች ኢኒሼቲቮች ጋር በማስተሳሰር ለመተግበር የሚደረገው ጥረት ስኬታማነት ሁሉም በጋራ እንዲረባረብ ጥሪ አቅርበዋል።

 

የኢፌ.ዴ.ሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የወጣቶች ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ ሙና አህመድ በበኩላቸው በ2015 በጀት አመት ባለፉት ዘጠኝ ወራት 24 ሚሊዮን በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን በ14 ዘርፎች በማሰማራት 53 ሚሊዮን የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ያደረጉ አገልግሎቶችን መስጠታቸውንና በዚህም ከ17 ቢሊዮን ብር በላይ ሀብት ማዳን መቻሉን ገልጸዋል።

 

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በጎ ፈቃደኛነት ለሀገር ግንባታ የሚኖረውን ፋይዳ በመገንዘብ በአሁኑ ወቅት ብሔራዊ የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ፓሊሲ እና የወጣቶች የዜግነት አገልግሎት አዋጅ የሚለከታቸው ባለድርሻና አጋር አካላት በተሳተፉበት አግባብ በረቂቅ ደረጃ በማዘጋጀት ጸድቆ በስራ ላይ እንዲውል ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

 


 

የአሊያንስ ኬር ፎር ናው /ACN/ መስራችና ዋና ስራ አስኪያጅ ወ/ሮ ናኦሚ ሀይሌ ፕሮጀክቱ በፓይለት ደረጃ ባለፉት ስድስት አመታት በአምስት የተለያዩ ቦታዎች ተግባራዊ ሲደረግ መቆየቱንና ውጤታማ ሆኖ በመገኘቱ ተደራሽነቱን ለማስፋት በጋራ ለመስራት ስምምነት ላይ በመደረሱ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።

 

በመርሃ ግብሩ ላይ የመንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የተባበሩት መንግስታት አጋር ድርጅቶች፣ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ ተወካዮች እንዲሁም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የተገኙ ሲሆን ፕሮጀክቱ ውጤታማ እንዲሆንም የበኩላቸውን እገዛ እንደሚያደርጉ በሰጡት አስተያየት አረጋግጠዋል።

Please follow and like us:

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *