ከድህነትና ተረጂነት ለመውጣት ሁሉም በየተሰማራበት በትጋት መስራት አለበት

“ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለተሟላ ሀገራዊ ክብር፣ ነጻነትና ሉዓላዊነት” በሚል መሪ ቃል ለተቋሙ ሰራተኞች ስልጠና ተሰጥቷል።

የስልጠናው ዋና ዓላማ በሀገራችን ስር ሰዶ የቆየውን የተረጂነትና የልመና አስተሳሰብ በማስወገድ ራስን ለመቻል በሚደረገው ጥረት ውስጥ የፌዴራል ተቋማት ሚና መለየትና መግባባት መፍጠር እንደሆነ ተጠቁሟል። በስልጠናው የተረጂነትና የጥገኝነት አመለካከት ሀገርን ለውርደት የሚዳርግ፣ ሉዓላዊ ክብርን ዝቅ የሚያደርግ፣ የፖሊሲ ነጻነትንም የሚያሳጣ፣ በአለም አቀፍ መድረክም አንገትን የሚያስደፋ መሆኑ ተነስቷል። የተረጂነትና የልመና አስተሳሰብ በማስወገድ በአዲስ አስተሳሰብና አሰራር መተካት እንዳለበትና እስካሁን የነበረውንም አካሄድ መለወጥ እንደሚያስፈልግ ተጠቁሟል። ሀገራችን ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ በመረዳት አስተሳሰቡን ከማስወገድ ባሻገር ጠንካራ የአደጋ ስጋት አመራር ስርዓት የእቅድ አካል የማድረግ ባህል ማጎልበትና ለችግሮች ሀገር በቀል መፍትሄ ማበጀት እንደሚገባ ተመላክቷል። እንደሀገር ከድህነትና ተረጂነት ለመውጣት የሰራተኛው፣ አመራሩና የእያንዳንዱ ዜጋ አስተዋጽዖው ከፍተኛ በመሆኑ ሁሉም በየተሰማራበት መስክ በትጋት መስራት እንዳለበትም ተገልጿል።

እንደተቋም በተለይ ከተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ጋር በተያያዘ ተጋላጭ የሆኑትን በጥንቃቄ በመለየት ተገቢውን ድጋፍ እንዲያገኙ ከማድረግ ጎን ለጎን ዜጎች ከገጠማቸው ጊዜያዊ ችግር ተላቀው በዘላቂነት የሚቋሙበትን አሰራር መዘርጋትና ከተረጂነት እንዲወጡ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ተጠቅሷል። በውይይቱ ላይ የተረጂነት አስተሳሰብ በግልም ሆነ በአገር ላይ የሚያደርሰው ጉዳትና መፍትሄዎቹ ላይ ውይይት በማድረግና ጠንክሮ በመስራት ሁሉም ሚናውን ለመወጣት ስምምነት ላይ ተደርሷል።

 

Please follow and like us: