በጎነትን ለማስረጽ እና የአብሮነት እሴቶችን ለማጎልበት የበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ሚና ከፍተኛ ነው ሲሉ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ሴቶች ህፃናት እና ወጣቶች ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ገነት መኩሪያ ገለፁ።

የ2016 የወሰን ተሻጋሪ የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልገሎት ተሳታፊዎች በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ዳውሮ ዞን የተለያዩ በጎ ተግባራትን አከናውነዋል።

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልላዊ መንግስት ሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ገነት መኩሪያ እንደገለፁት፤ ወሰን ተሻጋሪ የክረምት ወራት በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ሠላምን አስተማማኝና ዘላቂ ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን ውጤታማ እንዲሆኑ ሚናቸው የጎላ ነው ብለዋል። ጠንካራ ሀገረ መንግስት በመገንባት ኢትዮጵያን ወደ ቀደመ ከፍታዋ በመመለስ እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችን ይበልጥ ስኬታማ ለማድረግ የወጣቶችን ተሳትፎ ማስፋፋት ወሳኝ መሆኑንም ኃላፊዋ አስረድተዋል።

 

ወጣቶቹ የሀገራቸው ጠቃሚ ዕሴቶችን የሚያሳድጉበት፣ የህይወት ክህሎትን፣ ልምድና ባህሎችን የሚቀስሙበት ይኸው ሂደት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ቢሮው ከባለድርሻ አካላት ጋር ቅንጅታዊ አሰራሩን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል። ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሁሉ ለተግባሩ ቀጣይነትና ስኬታማነት ኃላፊነታቸውን በተገቢው እንዲወጡ ወ/ሮ ገነት ጠይቀዋል።

የታርጫ ከተማ ካንቲባ አቶ ዳዊት ወንድሙ በበኩላቸው የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ሰዎች ጊዜያቸውን፣ ገንዘባቸውን፣ ጉልበታቸውንና እውቀታቸውንና አምነው የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ነው ብለዋል። እንደ ታርጫ ከተማ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ያደረጉ በርካታ ሥራዎች በመሰራት ላይ ይገኛል ያሉት ካንቲባው ተግባሩን አጠናክሮ ለማስቀጠል አስተዳደሩ ያላሰለሰ ጥረት እያደረገ ነው ብለዋል። የዳውሮ ዞን ሴቶች፣ ህጻናት ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ ብርሃኔ ብሩ ወሰን ተሻጋሪ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በጎነትን ለማስረጽ እና አብሮነትን ለማጠናከር እያበረከቱት የሚገኘው የዜግነትን ኃላፊነት የሚደነቅ ነው ብለዋል።

በጎ አድራጊዎች ለሚኖሩበት ማህበረሰብ፣ ልማትና ለአካባቢ ደህንነት እያበሰከቱ ያለው አስተዋጽኦ ዘላቂ እንዲሆን ሁሉም መተባበር እንደሚገባም ኃላፊዋ አስገንዝበዋል። የዘንድሮ ወሰን ተሻጋሪ የክረምት ወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት “በጎነትና አብሮነት ለኢትዮጵያ ከፍታ!” በሚል መሪ ሀሳብ ለ3ኛ ጊዜ ከ14ቱ የስምሪት መስኮች መካከል የችግኝ ተከላ፣ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ላይ ግንዛቤ የመፍጠርና አካባቢ ጽዳት ሥራ በዳውሮ ዞን ተርጫ ከተማ ተከናውኗል።

Please follow and like us: