የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ከካፍ የስራ አስፈፃሚ አባል ሚስ ኢሻ ጆሃንሰን ጋር ተወያዩ

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ እና የጤና ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር መቅደስ ዳባ ከአፍሪካ እግር ኳስ ፌዴሬሽን(CAF) ስራ አስፈፃሚ አባል ሚስ ኢሻ ጆሃንሰን ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም የስራ ኃላፊዎቹ ስፖርት በተለይም እግር ኳስ በአካል የዳበረ፣ ጤናማና አምራች ዜጋ ለማፍራት ባለው ሚና፣ በዘርፉ የአፍሪካ ሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶችን ማብቃትና መደገፍ እንዲሁም በቀጣይ ትብብርን ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ በሰፊው መክረዋል በተጨማሪም የአብዛኛ አፍሪካውያን ሴቶች ጤናን እየጎዱ ያሉት ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ስርጭትን መከላከልና የጤና አገልግሎት ተደራሸነትን ማሳደግን ጨምሮ በሌሎች የትብብር መስኮች አጋርነትን ማጠናከር በሚያስችሉ ነጥቦች ላይ ፍሬያማ ውይይት አድርገዋል። የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ በዚሁ ጊዜ፥ በሀገሪቱ ያሉ የወጣቶች ሰብዕና ማዕከላት በተሟላ መልኩ አገልግሎት መስጠትና የተቋቋሙበትንም ዓላማ ማሳካት እንዲችሉ ፊፋ ድጋፍ እንዲያደርግና ማህበራዊ ኃላፊነቱንም እንዲወጣ ጠይቀዋል።

የካፍ ስራ አስፈፃሚ አባል ሚስ ኢሻ ጆሃንሰን በበኩሏ፥ ወደ ኢትዮጵያ ስትመጣ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑን አስታውሳ በተደረገላት አቀባበልና መስተንግዶ መደሰቷን ገልፃለች። ስፖርት የዜጎችን ትስስር ለማጠናከርና የማህበረሰብ ለውጥን ለማፈጠን ትልቅ መሣሪያ መሆኑን አንስታለች። በስፖርቱ ዘርፍ የደረሰችበትን ደረጃ፣ በእግር ኳስ ፌዴሬሽን ውስጥ ስላላት ሚና እንዲሁም በማህበረሰብ አገልግሎት ረገድ እያከናወነች ስላለው የበጎ አድራጎት ስራ የረጅም ጊዜ ልምዷን አካፍላለች። ሚስ ኢሻ በእርስ በእርስ ጦርነት ምክንያት በትውልድ ሃገሯ ሴራሊዮን ለተፈናቀሉና ለችግር ለተጋለጡ ሴቶችና ህፃናትን እንዲሁም ዝቀተኛ ገቢ ላላቸው ወገኖች ባቋቋመችው የበጎ አድራጎት ድርጅት ልዩ ልዩ ድጋፍ እንዲያገኙና ወደ ማህበረሰቡ እንዲቀላቀሉና እንዲቋቋሙ ሰብዓዊ ድጋፍ ማድረጓንና ስፖርትን እንደመሳሪያ መጠቀም መቻሏ ለስኬት እንዳበቃት ተናግራለች።

በተጨማሪም ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ሴቶች ላይ የሚደርሰውን የጤና ችግር ለመቅረፍ ፒንክ ቻሪቲ ፋውንዴሸ የተሰኘ የበጎ አድራጎት ድርጅት በሟቋቋም የግንዛቤና ንቅናቄ ስራዎችን ስትሰራ መቆየቷም ተጠቅሷል። ሚስ ኢሻ ጆሃንሰን የቀድሞ የሴራሊዮን የእግር ኳስ ማህበር ፕሬዝደንት፣ የፊፋ ምክር ቤት ብሎም የካፍ ስራ አስፈፃሚ አባል፤ በስራ ፈጠራ ረገድም የመጀመሪያዋ የአፍሪካ ሴት የእግር ኳስ ክለብ መስራችና ባለቤት እስከመሆን የደረሰች ጠንካራ እንስት መሆኗ ለሌሎች የአፍሪካ ሴቶች አርአያና ተምሳሌት ሆና በጉልህ ትጠቀሳለች። በቀጣይም የባለብዙ ወገን ትብብርን በይበልጥ ማጠናከርና ማሳደግ እንደሚገባ በውይይቱ ወቅት ተገልጿል።

 

Please follow and like us: