” የማህበራዊ አገልግሎቶች አካል ጉዳተኞችን አካታችና ይበልጥ ተደራሽ ያደረጉ እንዲሆኑ በቅንጅት እንሰራለን” – ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሁሪያ አሊ

የማህበራዊ አገልግሎቶች አካል ጉዳተኞችን አካታችና ይበልጥ ተደራሽ ያደረጉ እንዲሆኑ በቅንጅት እንሰራለን ሲሉ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሁሪያ አሊ ገለፁ።

የአለም አቀፍ አካል ጉዳተኞች ቀን ማጠቃለያ እና የፕራይድ ዓመታዊ ክብረ በዓልን ምክንያት በማድረግ የልምድ ልውውጥ መድረክ እየተካሄደ ይገኛል።በመድረኩ ላይ የተገኙት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሁሪያ አሊ ኢትዮጵያ የአካል ጉዳተኞችን መብት ለማስከበር ብሎም በሁሉም መስክ ያላቸውን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያግዙ አበረታች እርምጃዎች እየወሰደች መሆኗን ተናግረዋል።

ለአካል ጉዳተኞች የተመቹ መሠረተ ልማቶችን ማስፋፋትና ተደራሽ ማድረግ፣ አካታች ፖሊሲዎችን መቅረፅ፣ የተሃድሶ አገልግሎት መስጫ ተቋማትን ማጠናከር እንዲሁም የስራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ በቁርጠኝነት መስራት ይገባል ብለዋል።

ለዚህም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እንደ ትምህርት፣ ጤና ያሉ መሠል የማህበራዊ አገልግሎቶች አካል ጉዳተኞችን አካታችና ተደራሽ ያደረጉ እንዲሆኑና ያለባቸውም ችግር በዘላቂነት እንዲፈታ በቅንጅት እንሰራለን ብለዋል።

አካል ጉዳተኞች ያላቸውን እምቅ አቅም አውጥተው እንዲጠቀሙና ህልማቸውን እውን እንዲያደርጉ ድጋፍ እያደረጉ ያሉ አካላትን አመስግነው የትብብር ስራው ተጠናክሮ እንዲቀጥልም በአፅዕኖት አሳስበዋል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የአካል ጉዳተኞች መብቶች በአግባቡ እንዲታወቁና እንዲከበሩ የግንዛቤና አድቮኬሲ ስራዎችን በትኩረት እየሰራ ይገኛል።

 

Please follow and like us: