Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
የአካቶ ትግበራ ስራዎችን ለማጠናከር የፌደራል ተቋማትና ዩኒቨርሲቲዎች በቅንጅትና በትብብር መስራት እንደሚገባ ተገለፀ።
በፌዴራል ተቋማት እና በመንግስት ዩኒቨርስቲዎች የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች አካቶ ትግበራ ፎረም የውይይት እና የልምድ ልውውጥ የጋራ የምክክር መድረክ በመካሄድ ላይ ነው።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ በመድረኩ እንደገለፁት፤ የሴቶችን፣ የህጻናትን፣ የወጣቶችን፣ የአካል ጉተኞችን፣ የአረጋውያንና ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎችን ሁለንተናዊ መብትና ደህንነት ባስጠበቀ መልኩ ተሳትፎና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በሚያስችል መልኩ ጉዳዩ በቀጥታ ከሚመለከታቸው መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር በተቀመጡ የፖሊሲና ስትራቴጂክ እርምጃዎች ላይ ከወረቀት በዘለለ በትብብርና በቅንጅት መስራት እንደሚገባ ገልፀዋል።
ፎረሙ የእነዚህን የህብረተሰብ ክፍሎች መብት፣ ደህንነት፣ ተሳትፎና ተጠቃሚነት የሚረጋገጥበት ስርዓት ዝርጋታን ማጠናከርን ማዕከል ያደረገም ነው ብለዋል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም ሁሉም ተቋማት የአካቶ ትግበራ ስራዎች ውጤታማ የሚሆኑበትን መደላድል ለመፍጠር እንዲቻል ክፍተትን መሰረት ያደረጉ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን እየተሰጠ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም የተቋማት የአካቶ ትግበራ ስራ የአፈጻጸም ደረጃን ለመለካት የሚያስችል የምዘና ማዕቀፍ በማዘጋጀት ባለፉት ጊዜያት ሚኒስቴር መ/ቤቶችን በመመዘን የተሻለ አፈፃፀም ላመጡ ተቋማት ዕውቅና መስጠቱን አስታውሰዋል።
በቀጣይም አካታች የመመዘኛ ማዕቀፍ በማዘጋጀት ተጠሪ ተቋማትን ለመመዘን እና ደረጃ ለመለየት ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
የአካቶ ትግበራ የተቋማት ተጠያቂነት ማረጋገጫ ረቂቅ ደንብ የአካቶ ትግበራ ስራን በተሰጣቸው ተግባርና ኃላፊነት ልክ በማይተገብሩና ጉልህ የአፈጻጸም ክፍተት ያለባቸውን ተቋማት ተጠያቂ ለማድረግ የሚያስችል መሆኑንም ጠቅሰዋል።
የምዘናው ዋና ዓላማ ተቋማት በአካቶ ትግበራ የተሻለ አፈጻጸም እንዲኖራቸውና ስርነቀል ለውጥ እንዲመጣ ማድረግን ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡
