“በወጣቶች ላይ ኢንቨስት እናድርግ፤ ለሁሉም ሰላምና ብልጽግና የሰፈነባት ሀገር ለመገንባት በጋራ እንስራ” – ክብርት ሚኒስትር ዴኤታ ሙና አህመድ

“ወጣት የሰላም ባለቤት” በሚል መሪ ሃሳብ ሀገር አቀፍ የወጣቶች የሰላምና ደህንነት ኮንፈረንስ በስካይላይት ሆቴል እየተካሄደ ይገኛል።

በመድረኩ ላይ ለተገኙ እንግዶችን የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የወጣቶች ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሙና አህመድ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ወጣቶችን ማብቃት ላይ ያተኮሩ በርካታ ስራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል ብለዋል።

ሆኖም የግጭት መንስኤ የሆኑት የተሳትፎ ዕድሎች፣ ኢ-ፍትሃዊነት፣ ስራ አጥነት፣ የስብዕና ግድፈት፣ ማህበራዊ መገለል እና የመሳሰሉ ችግሮችን መፍታት ለዘላቂ ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።

ለዚህም በስራ ፈጠራ፣ በስብዕና ግንባታ፣ በማህበራዊ አገልግሎቶች፣ የወጣት አደረጃጀቶችን በማጠናከር፣ ወጣቶች የውሳኔ ሰጭነት ሚናቸው እንዲጎለብት በመደገፍ እንዲሁም ወጣቶች ትርጉም ያለው ተሳትፎ እንዲኖራቸው በማድረግ ለወጣቶች ዕድሎችን ለመፍጠር በርካታ ስራዎችን በመስራት ላይ እንገኛለን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ የወጣቶች የሰላምና ደህንነት የድርጊት መርሐ-ግብር መዘጋጀት ሀገራችን ወደ ዘላቂ ሰላምና ብልጽግና ለምታደርገውን ጉዞ አዲስ ምዕራፍ ነው ሲሉ ገልፀዋል።

“በወጣቶች ላይ ኢንቨስት እናድርግ፤ ለሁሉም ሰላምና ብልጽግና የሰፈነባት ሀገር ለመገንባት በጋራ እንስራ” ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመድረኩ ላይ የተገኙ የአለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች የወጣቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንዲሁም በሰላም ግንባታ ረገድ ያላቸውን ሚናና ተሳትፎ ለማሳደግ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልፀዋል።

Please follow and like us: