Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
እንግሊዝ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነትን ለማጠናከርና በጋራ ለመሥራት እንደምትፈልግ አስታወቀች
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ ከእንግሊዝ አምባሳደር ዳረን ዌልች እና ከፍተኛ ልዑክ ቡድናቸው ጋር የሁለትዮሽ ግንኙነትን የበለጠ ማጠናከርና በትብብር መሥራት በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ፍሬያማ ውይይት አካሄዱ። ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች በተለይ በማህበራዊ ጥበቃና አካታችነት፣ የሴቶችን መብትና የስርዓተ ፆታ እኩልነት፣ ሴቶች በሰላም ግንባታና ግጭት አፈታት ረገድ ያላቸው አስተዋፅዖ፣ ሴቶችን በኢኮኖሚ ማብቃት እንዲሁም የሴት ልጅ ግርዛትንና ፆታን መሠረት ያደረገ ጥቃቶችን በመከላከል ዙሪያ ተወያይተዋል።

በውይይታቸው፥ ክብርት ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጎጌ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሃላፊነት ሰፊ መሆኑንና የሴቶች፣ የህፃናትና የወጣቶችን እንዲሁም የአካል ጉዳተኞች፣ አረጋውያንና ሌሎች ለችግር ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ጉዳይ የተመለከቱ በርካታ ተግባራትንም እያከናወነ እንደሚገኝ በሰፊው አብራርተዋል። ዩናይትድ ኪንግደም መንግስት እና የእንግሊዝ ኤምባሲ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በኢትዮጵያ ለሚከናወኑ የማህበራዊ ጥበቃ፣ የስርዓተ ፆታ እኩልነትና በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎችን ለማብቃት እያደረጉት ላለው ድጋፍ ከፍ ያለ አድናቆትና ምስጋና አቅርበዋል።

ሆኖም በማህበረሰቡ ዘንድ ያለው የተዛባ አመለካከት፣ የመረጃ እጥረትና የሀብት ውስንነት መኖሩ የስርዓተ ፆታ እኩልነት አለመስፈኑ ትልቅ ተግዳሮት መሆኑንና ችግሩን ለመፍታት በጋራ መስራት አስፈላጊ መሆኑን ገልፀዋል። የእንግሊዝ አምባሳደር ዳረን ዌልች በበኩላቸው፥ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከተሰጠው ሃላፊነት አንፃር ሰፋፊ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን በመግለፅ አድንቀዋል።
በቀጣይም አጋርነት የበለጠ ለማጠናከር፣ በተጠቀሱትና በሌሎችም መስኮች በትብብር ለመሥራት ሀገራቸው እንደምትፈልግ አምባሳደሩ ገልፀዋል።
