Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
የዜጎችን ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታትና ህይወታቸውን ለመለወጥ የሚደረገው ጥረት ውጤታማ እንዲሆን በጥናትና ምርምር ሊደገፍ ይገባል — ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ
15ኛው አመታዊ የህፃናት፣ ሴቶችና ወጣቶች ምርምርና ትግበራ ፎረም አውደ ጥናት እየተካሄደ ይገኛል።

በአውደ ጥናቱ ላይ የተገኙት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተለያዩ ፖሊሲዎችን፣ ስትራቴጂዎችንና ፕሮግራሞችን በመንደፍ ለዜጎች ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት የሚያስችሉ በርካታ ስራዎችን በቅንጅት እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።
ሆኖም ሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶችን ጨምሮ ለችግር ተጋላጭ የሆነ የማህበረሰብ ክፍሎችን ችግሮች ደረጃ በደረጃ ለመፍታትና ህይወታቸውን በዘላቂነት ለመለወጥ የሚደረገው ጥረት የበለጠ ውጤታማ እንዲሆን በጥናትና ምርምር ሊደገፍ ይገባል ብለዋል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በፎረሙ አማካኝነት እየተካሄዱ ያሉ የጥናትና ምርምር ውጤቶችን በግብዓትነት እየተጠቀመበትና ድጋፍ ሲያደርግም መቆየቱን ተናግረዋል። ፎረሙን እንዲመሰረት ሀሳብ ከማፍለቅ ጀምሮ በማስተባበር፣ በመደገፍ እና በጥናትና ምርምር ስራዎች ላይ ጉልህ አስተዋፅዖ ላበረከቱ ባለድርሻና አጋር አካላት ሁሉ የላቀ ምስጋና አቅርበዋል። ፎረሙ በመረጃ ላይ የተመሠረተ የፖሊሲ አቅጣጫዎችን እና ሊተገበሩ የሚችሉ ሃሳቦችን የሚያመነጭ በመሆኑ ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ክብርት ሚኒስትሯ አረጋግጠዋል።

የዩኒሴፍ ኢትዮጵያ ተወካይ ዶ/ር አቡበከር ካምፖ በበኩላቸው፥ ፎረሙ በጥናትና ምርምር ላይ የተሰማሩ ምሁራን እንዲሁም በሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ዙሪያ የሚሰሩ ተቋማት በጋራ ተገናኝተው የሚወያዩበትና የሚመክሩበት መድረክ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል ብለዋል።

የያንግ ላይቭስ ኢትዮጵያ ዳይሬክተር እና የፎረሙ አስተባባሪ ዶ/ር አሉላ ፖንከረስት በበኩሉ ባለፉት 15 አመታት ለተለያዩ ፖሊሲና ስትራቴጂ ግብዓት የሚሆኑ ከ 173 በላይ የጥናትና ምርምር ስራዎች መካሄዳቸውን ገልፀዋል። በፎረሙ በወጣቶችና አፍላ ወጣቶች፣ በያለዕድሜ ጋብቻ፣ በግርዛት፣ በስርዓተ ፆታ እኩልነት፣ በህፃናት ጉልበት ብዝበዛ፣ በስደት እና በሌሎችም ላይ ትኩረት ያደረጉ ርዕሰ ጉዳዮች መዳሰሳቸውን ጠቁመዋል።
በቀጣይም ፎረሙ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ዩኒሴፍና ዩኤን ውመን ኢትዮጵያ እና ሌሎችም ድጋፍ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል። በዕለቱ የምርምር ውጤቶች ቀርበው በተሳታፊዎች ሰፊ ውይይት እየተካሄደ ይገኛል።
