Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
በዘላቂ ሰላም ግንባታና የቤተሰብ የኑሮ ሁኔታ ማሻሻያ ፕሮግራም ትግበራና ስኬታማነት ዙሪያ ፍሬያማ ውይይት መካሄዱ ተገለፀ
ዘላቂ ሰላምን ለመገንባትና የቤተሰብ የኑሮ ሁኔታን ለማሻሻል በተቀረፀው ፕሮግራም ትግበራና ተያያዥ ጉዳዩች ዙሪያ ፍሬያማ ውይይት መካሄዱን የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ ገለፁ።

ክብርት ሚኒስትሯ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ፥ ካላፈው አመት ጀምሮ በተለይ በትግራይ፣ አማራና አፋር ክልሎች ዘላቂ ሰላም ለማስፈንና ሂደቱን ለማሳለጥ የሚረዳ ኢኒሼቲቭ / Peace Support Facilitation Program/ ተነድፎ ወደ ትግበራ መግባቱን ተናግረዋል። እየተተገበረ ያለውን የሰላም ግንባታ ሂደት ለመደገፍና ለማስተባበር የሚያስችል ብሔራዊ ስቲሪንግ ኮሚቴ መቋቋሙንና ቀደም ሲልም በጉዳዩ ዙሪያ ሰፊ ውይይት ሲደረግና የተለያዩ ተግባራትም ሲከናወኑ መቆየቱን አስታውሰዋል።

በ2025 የፕሮግራሙ ሁለተኛ ምዕራፍ ትግበራ በተመረጡ 22 ወረዳዎች እንደሚካሄድ ክብርት ሚኒስትሯ ጠቁመው፥ ውይይቱ በአተገባበሩ ዙሪያ ያተኮረ መሆኑንም አንስተዋል። ፕሮግራሙ በዋነኝነት በአካባቢዎቹ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን እና በግጭት ምክንያት ግንባር ቀደም ተጎጂ የሆኑትን ሴቶች፣ ህፃናትና ሌሎች ለችግር ተጋላጭ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎችን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻልና የበለጠ ተጠቃሚ ለማድረግ ያለመ መሆኑን በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ገልጸዋል።
በተጠቁሱት አካባቢዎች ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የሚደረገውን ጥረት በመደገፍ ረገድ የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም/UNDP/ እንዲሁም የጀርመን፣ የጃፓን እና የኔዘርላንድ መንግስት እያበረከቱት ላለው አስተዋፅዖ ክብርት ሚኒስትሯ ምስጋና አቅርበዋል።
