ፖሊሲው ሁሉን አቀፍ፣ አካታችና የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን ባህል ያደረገ ዜጋ ለመፍጠር በሚያስችል መልኩ እየተዘጋጀ ነው – ክብርት ሙና አህመድ

የኢፌዴሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ቪ ኤስ ኦ/VSO/ ከተሰኘ አለም አቀፍ የበጎ አድራጎት ድርጅት ጋር በመተባበር በረቂቅ ብሔራዊ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ፖሊሲ ላይ ግብዓት ለማሰባሰብ የሚያስችል መድረክ አካሂዷል።

በመድረኩ የወጣቶች ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሙና አህመድ እንደገለፁት፥ የሀገር ብልጽግናን ለማፋጠንና የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መንግስት በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።

ይህን እውን በማድረግ ረገድ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ድርሻው የጎላ ነው ብለዋል።

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ወጥና ተደራሽ በሆነ መልኩ የሚሰጥበትን ሁኔታ መፍጠር ደግሞ የተቋሙ አንዱና ዋነኛ ተግባር መሆኑን ተናግረዋል።

በ1996 ዓ.ም የወጣውን ብሔራዊ የወጣቶች ፖሊሲ መነሻ በማድረግ እየተካሄደ ባለው የንቅናቄ ስራ አገልግሎቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገና በርካታ ዜጎችንም ተጠቃሚ እያደረገ መምጣቱን አንስተዋል።

ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አስተሳሰብና ተግባርን ባህል ያደረገ ዜጋ ለመፍጠር በትኩረት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።

ለዚህም አገልግሎቱን በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች በተቀናጀ አግባብ ተደራሽ ለማድረግ ያለመ ብሔራዊ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ፖሊሲ ተቀርፆ በየደረጃው ውይይት ሲደረግበት መቆየቱንና ለፕላንና ልማት ሚኒስቴር ጭምር ግብዓት እንዲሰጥበት መቅረቡን አስታውቀዋል።

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰብዓዊነት ላይ ተመስርቶ የሚከወን ተግባር እንደመሆኑ፥ ፖሊሲው ከወጣቶች ባሻገር በሁሉም የዕድሜ ክልልና የስራ ዘርፍ ያሉ ዜጎች የሚሳተፉበትና ሌላውን የህብረተሰብ ክፍል መጥቀም የሚችሉበትን ዕድል ይዞ መምጣቱን ተናግረዋል።

ፖሊሲው በጎ ፈቃደኞች ላከናወኗቸው ስራዎች ከምስጋና ጀምሮ የሚሰጣቸው የተለያየ ዕውቅና ዋጋ እንደሚኖረውና በተለይም በስራ ቅጥርና በማህበራዊ አገልግሎቶች ቅድሚያ የሚያገኙበት አሰራርን ማካተቱን አመልክተዋል።

በተለያዩ አካላት የሚሠጡ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዕድገት ያላቸውን አበረክቶ በአግባቡ መለካት የሚያስችል ስታንዳርድ/መስፈርት/ እየተዘጋጀ እንደሆነም ክብርት ሚኒስትር ዴኤታዋ ጠቁመዋል።

የቪ ኤስ ኦ ኢትዮጵያ ፕሮግራም ዳይሬክተር አቶ ተመስገን አለሙ በበኩላቸው፥ ድርጅቱ ለፖሊሲው ዝግጅት ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱ ገልፀው በቀጣይም ፀድቆ በስራ ላይ እንዲውል አስፈላጊው እገዛ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

ረቂቅ ፖሊሲውን ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የማኔጅመንት አባላት ያቀረቡት የጥናት ቡድኑ አባል ወጣት ሀብታሙ ከበደ፥ ፖሊሲውን ማዘጋጀት ስለአስፈለገበት ምክንያት፣ ዓላማውና በውስጡ ስለተካተቱ አንኳር ጉዳዮች እንዲሁም ስለማስፈፀሚያ ስልቱ በዝርዝር አብራርተዋል።

ሰነዱን መነሻ በማድረግ ተሳታፊዎች ባነሷቸው ጥያቄዎችና አስተያየቶች ዙሪያ ውይይት ተካሂዷል።

 

Please follow and like us: