ኢትዮጵያ በሴቶችና ልጃገረዶች ላይ የሚፈፀመውን ጎጂ ልማዳዊ ድርጊትና ፆታዊ ጥቃት ለማስቆም በትኩረት እየሰራች ነው – ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ

የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ኤርጎጌ ተስፋዬ ( ዶ/ር) ኢትዮጵያ በሴቶችና ልጃገረዶች ላይ የሚፈፀመውን ጎጂ ልማዳዊ ድርጊትና ፆታዊ ጥቃትን ለማስቆም በትኩረት እየሰራች መሆኑን ገለፁ።

ክብርት ሚኒስትሯ ይህንን የገለጹት የኢትዮጵያን ጥረቶች እና ስኬቶች አስመልክቶ የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከGAGE, UNFPA እና UNICEF ጋር በመተባበር ‘በሴቶችና በታዳጊ ልጃገረዶች ላይ የሚፈፀመውን ጥቃት ለማስቆም ያሉ አስቻይ ሁኔታዎችና የቀጣይ አቅጣጫ’ በሚል ባዘጋጀው የጎንዮሽ መድረክ ላይ ባስተላለፉት መልእክት ነው። ክብርት ሚኒስትሯ በመልዕክታቸው፥ ኢትዮጵያ በሴቶችና ልጃገረዶች ላይ የሚፈፀመውን ጎጂ ልማዳዊ ድርጊትና ፆታዊ ጥቃትን ለማስቆም የሚያስችሉ የአሰራር ማዕቀፎችን በመቅረፅ በስራ ላይ ማዋሏን ገልፀዋል። ቀደም ሲል የነበረው ብሔራዊ የሴቶች ፖሊሲ ሴቶችን ለማብቃትና የስርዓተ ፆታ እኩልነትን ለማረጋገጥ በሚያስችል መልኩ እንደአዲስ እየተቀረፀ መሆኑን ገልፀው፥ ጥቃትን የማስቆም ጉዳይ በፖሊሲው ውስጥ ልዩ ትኩረት ማግኘቱን ጠቁመዋል።ከዚሁ ጎን ለጎን ድርጊቱን አስቀድሞ ለመከላከል እንዲያስችል የማንቃት ስራ ከመሰራቱም በላይ የጥቃት ተጎጂዎች የተቀናጀ የጤና፣ የፍትህ፣ የሥነ-ልቦናና የማህበራዊ ድጋፍ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ የአንድ ማዕከልና የተሃድሶ አገልግሎት መስጫ ማዕከላትን የማቋቋምና የማጠናከር ስራ ከአጋር ድርጅቶች ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።

እየተደረገ ባለው ጥረት አበረታች ውጤት እየተመዘገበ ቢሆንም ድርጊቱን ሙሉ በሙሉ ለማስቆም አሁንም ሰፊ ስራ ይጠይቃል ብለዋል።የጥበቃ ስርዓቱን ከማጠናከር በተጨማሪ ተጎጂዎች ፍትህ እንዲያገኙና የሚሰጡ አገልግሎቶችንም ተደራሽነት ለማሳደግ በቅንጅት መረባረብ አንደሚገባ ገልጸው አለም አቀፍ ተቋማት፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችና የሚመለከታቸው አካላት ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት ሰጥተው እንዲመክሩና ለችግሩ ዘላቂ መፍትሔ እንዲያመላክቱ ጥሪ አቅርበዋል።

በሥርዓተ-ፆታ እኩልነት እና በሴቶች ልማት ላይ ትኩረቱን ባደረገውና በአሜሪካ ኒው ዮርክ እየመከረ ባለው ጉባኤ ላይ የኢትዮጵያ ልዑካን እየተሳተፉ ይገኛል።

Please follow and like us: