ኢትዮጵያ የፓንአፍሪካ ወጣት አመራሮች ጉባኤ ልታካሂድ ነው – ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ

ኢትዮጵያ በአህጉር አቀፍ ደረጃ በአይነቱ ልዩ እና የመጀመሪያ የሆነውን የፓን አፍሪካ ወጣቶች አመራር ጉባኤ ልታካሂድ መሆኑን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ ገለፁ።

ሚኒስቴሩ በቅርቡ ሊካሄድ ስለታሰበው የፓንአፍሪካ ወጣት አመራሮች ጉባኤ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል። በመግለጫው፥ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ በሀገራችንም ሆነ በአህጉሪቱ በሚካሄደው ሁሉን አቀፍ የለውጥ እንቅስቃሴ ውስጥ ወጣቶች አይተኬ ሚናቸውን እንዳላቸው ገልፀዋል። ወጣቶችም ሆኑ አህጉሪቱ እያጋጠሟት ያሉትን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተግዳሮቶች በብቃት ለመፍታት ብሎም የበለፀገች፣ ሰላሟ የተጠበቀና የምንመኛትን አፍሪካን ለመፍጠር በአጀንዳ 2063 የተቀመጠው ራዕይ እውን እንዲሆን ወጣቶች ትልቅ አቅም እንዳላቸው ገልፀዋል።

“ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ” በማበጀት ረገድ የፓንአፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ ጉልህ ስፍራ እንዳለው የጠቀሱት ክብርት ሚኒስትሯ ኢትዮጵያ ለፓንአፍሪካኒዝም መስዋዕትነት መክፈሏንና የነፃነት ተምሳሌት መሆኗን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅትም ሚኒስቴሩ በአፍሪካ ወጣቶችና ወጣት አመራሮች ዘንድ የፓን አፍሪካኒዝም አስተሳሰብ ለማስረፅ ከአፍሪካ ህብረትና ከሚመለከታቸው አስፈፃሚ አካላት ጋር በመተባበር በአህጉር አቀፍ ደረጃ የመጀመሪያ የሆነውን የፓን አፍሪካ ወጣት አመራሮች ጉባኤ ለማካሔድ ቅድመ ዝግጀት በማጠናቀቅ ላይ መሆኑን ጠቁመዋል።

ጉባኤው ወጣት መሪዎቿ በችግሮቻቸውና መፍትሔው ዙሪያ በጋራ ተገናኝተው በነፃነት የሚመክሩበት፣ ልምድና ተሞክሮዎቻቸውን የሚለዋወጡበት፣ አጋርነትን የሚያጠናክሩበት፣ የአህጉሪቱን እጣ ፈንታ በሚወስኑ አንኳር ጉዳዮች ላይ የቀጣይ አቅጣጫ የሚያስቀምጡበትንና አፈፃፀሙን የሚገመግሙበት መድረክ ሆኖ ያገለግላል ብለዋል።

ጉባኤው ከመጋቢት 25-27 ቀን 2017 ዓ.ም በአድዋ ድል መታሰቢያ አዳራሽ በተለያዩ መርሐግብሮች ለማካሄድ መታቀዱን ገልፀው የሚዲያ አካላት የፓንአፍሪካን እሳቤ ከማስረፅ ጀምሮ ለሀገሪቱ ገፅታ ግንባታ፣ የተዛቡ ሀገራዊና አህጉራዊ ትርክቶችን ለማረምና እየተሰሩ ያሉ ስራዎችንም አጉልቶ ለማሳየት የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

በጉባኤ ከሁሉም የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ ወጣት አመራሮችና የወጣቶች ጉዳይ ሚኒስትሮች፣ ምሁራን ወጣቶች፣ ወጣት የማህበረሰብ አንቂዎች፣ ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችና ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች እንደሚሳተፉ ጠቁመዋል።

ሚኒስቴሩ የወጣቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ለሀገሪቱም ሆነ ለአህጉሪቱ ሰላምና ብልፅግና የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉና የበኩላቸውንም ሃላፊነት እንዲወጡ ለማስቻል ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ይሰራል ብለዋል፡፡

 

Please follow and like us: