Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
ቀደምት አፍሪካውያን ለነፃነትና ለእኩልነት የከፈሉትን ዋጋ ወጣቱ በጥበብና በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ልማትና ሰላም በማስመዝገብ ሊደግመው ይገባል -ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ
ቀደምት አፍሪካውያን ለነፃነትና ለእኩልነት የከፈሉትን ዋጋ ወጣቱ በጥበብና በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ልማትና ሰላም በማስመዝገብ ሊደግመው እንደሚገባ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ ገለፁ።
በአዲስ አበባ ዓድዋ ድል መታሰቢያ እየተካሄደ በሚገኘው የፓን አፍሪካ ወጣቶች አመራር ጉባኤ ላይ ፕሬዝዳንት ታዬ ባስተላለፉት መልዕክት፤ አፍሪካ ራሷን ከቅኝ ግዛት ለማላቀቅ ለነፃነትና ለእኩልነት ታግላለች ብለዋል። ይህ ትግል በታላላቅ የአፍሪካ መሪዎች ውጤት ማምጣቱን ገልፀው፤ ለአፍሪካ ህብረት መመስረትም መነሻ እንደነበር አስታውሰዋል። የአፍሪካ አባቶች ለነፃነትና ለእኩልነት የከፈሉትን ዋጋ ወጣቱ በጥበብና በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ልማትና ሰላም በማስመዝገብ ሊደግመው ይገባል ነው ያሉት።

ስራ አጥነት፣ የአየር ንብረት ለውጥና የፖለቲካ አለመረጋጋትን ለመፍታት ወጣቶች በዕውቀትና በጥበብ የታገዘ እገዛ መስጠት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል። ወጣት አመራሮች ተለዋዋጭ ለሆነው የዓለም ጂኦ ፖለቲካ የሚመጥን ሀሳብ ማፍለቅና ውሳኔ መስጠት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል። ለአፍሪካ የሚያስፈልጋት ትብብርና በጋራ መስራት መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህ ረገድ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) የመደመር እሳቤን ተግባራዊ ማድረግ ውጤታማ ያደርጋል ብለዋል። ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን አሉታዊ ተፅዕኖ ለመቋቋም የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብርን ተግባራዊ ማድረግ መጀመራን፣ በምግብ ራስን ለመቻል የሌማት ትሩፋት መርኃ ግብር ተግባራዊ በመደረጉ በርካታ ውጤቶችን እያስመዘገበች መሆኗን ተናግረዋል።

የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ እውን እንድትሆን የምንፈልጋትን አፍሪካ ለመገንባት በፓን አፍሪካኒዝም እሳቤ የታነፀን ወጣት መሪ መገንባት ይገባል ብለዋል። ፓን አፍሪካኒዝም እርስ በርስ የተሳሰረችና የበለፀገች አፍሪካን እውን የሚያደርግ እሳቤ እንደመሆኑ ወጣቱ በዚህ መንፈስ ለአህጉሪቱ ልማትና ሰላም እንዲሰራ ጠይቀዋል። በአፍሪካ ህብረት የወጣቶች ልዩ መልዕክተኛ ቺዶ ፔምባ ወጣት አመራሮች አህጉሪቱን እየፈተኑ ያሉ ችግሮችን በተቀናጀና በተባበረ ክንድ ለመፍታት በጋራ የምንቆምበት ወሳኝ ጊዜ ላይ እንገኛለን ብለዋል።
የወጣቶችን ተጠቃሚነትና ተሳትፎ ለማሳደግ የወጡ ስትራቴጂዎች ከጠረጴዛ ወርደው ወደ ተግባር እንዲቀየሩ ወጣቶች በቁርጠኝነት እንዲሰሩም ጠይቀዋል። የአፍሪካን ዕጣ ፈንታ ያለማንም ጣልቃ ገብነት ለመወሰን የተባበረና የተቀናጀ ስራ ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።
