ቻይና እና ኢትዮጵያ በማህበራዊ ጥበቃ ዙሪያ ያላቸውን ጠንካራ ግንኙነትና ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር በጋራ እንደሚሰሩ ተገለፀ

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ሚስተር ቸን ሃይ እና ልዑክ ቡድናቸውን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

የስራ ሃላፊዎቹ በማህበራዊ ጥበቃና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ፍሬያማ ውይይት አካሂደዋል። በሂደት ላይ ያሉና የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳዮችን የተመለከቱ ዋና ዋና የአጋርነት ስራዎችን የበለጠ ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይም ሰፊ ውይይት አድርገዋል። በውይይቱ ወቅት ክብርት ሚኒስትሯ፥ ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር ያላትን ሁሉን አቀፍ የትብብር ስራዎች ያደነቁ ሲሆን በተለይም በማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ያለው አጋርነት ትልቅ ምሳሌ ሊሆን እንደሚችል ጠቅሰዋል። ቻይና በተለይም በቻይና ብሔራዊ የገጠር ልማት ፋውንዴሽን በኩል ለማህበራዊ ጥበቃ ለምትሰጠው ድጋፍ ክብርት ሚኒስትሯ ምስጋና አቅርበዋል።

በቀጣይም የቻይና ካምፓኒዎች ማህበራዊ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ለማስቻል ቀደም ሲል የተጀመረው ፕሮግራም በኢትዮጵያ ተጠናክሮ በሚቀጥልበት አግባብ፣ ከሆናን ፕሮቪንስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ተቋም ጋር የተፈረመው የመግባባቢያ ሰነድ አተገባበር እንዲሁም ከቻይና ሴቶች ፌዴሬሽን ጋር ያለውን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገርን በተመለከተ በሰፊው መክረዋል። በተጨማሪም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከቻይና ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና ከኢፌዴሪ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በጋራ ለመስራት እንዲያስችል በሂደት ላይ ያለውን የስነልቦና እና የአካል ጉዳተኝነት ፈጠራ ላብራቶሪ የመግባቢያ ሰነድ ማጠናቀቅ ላይም ሃላፊዎቹ ተወያይተዋል።

በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ሚስተር ቸን ሃይ በበኩላቸው ቻይና ለማህበራዊ ጉዳዮች ከፍተኛ ትኩረት እንደምትሰጥ ጠቅሰው ከኢትዮጵያ ጋር በዘርፋ ያላትን አጋርነት እንደምታጠናክርና ድጋፋ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል። ከዚሁ ጋር በተያያዘም በመጪው ነሐሴ በሚካሄደው የወጣቶች ፎረም ላይ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር እንዲገኙ አምባሳደሩ ኦፊሴላዊ ግብዣ አቅርበዋል።

 

Please follow and like us: