Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
ባገኘናቸው ስኬቶች ሳንዘናጋ የተጀመረው ለውጥ ቀጣይነት እንዲኖረው ሌት ተቀን በትጋት መስራትና የድርሻን መወጣት ይገባል -ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሙና አህመድ
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አመራሮችና ሠራተኞች የመሀሉ ዘመን ሰነድ ላይ ውይይት አካሂደዋል።

በመድረኩ የወጣቶች ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሙና አህመድ “ከወለሉ ወደ አፋፉ ለመውጣት ጉዞ ጀምረናል፤ አፋፍ ላይ ለመድረስ የሚደረገው ጉዞ ደግሞ ዕድልም ስጋትም አለው” ብለዋል። እንደሀገር ባለፉት አመታት በበርካታ ፈተናዎች ታጅበንም ቢሆን በተለያዩ መስኮች አንፀባራቂ ለውጥ መምጣቱንና የሁሉም አካላት አስተዋፅዖ ከፍተኛ እንደነበር አስታውሰዋል። እንደሴክተር በተለይ የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን በማሳደግ፣ የስርዓተ ፆታ እኩልነትን በማስፈን፣ የአካታችነት ስርዓትን በማረጋገጥ ረገድ የተደረጉ ጥረቶቾና የተገኙ ውጤቶች ማሳያ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ይሁንና ስኬቱ ልንደርስ ካሰብንበት ደረጃ አንፃር ሲታይ ጅምር መሆኑንና ብዙ መስራት እንደሚጠይቅ አንስተዋል። ለዚህም ሁሉም ተቋማዊና ሀገራዊ እንዲሁም አህጉራዊና አለም አቀፋዊ ሁኔታውን በጥልቀት መረዳትና ለረጆሙ ጉዞ ራሱን ማዘጋጀት ይኖርበታል ብለዋል። የብልፅግና ራዕይና ህልምን እውን ለማድረግ ሁላችንም ዘመኑን የዋጀ ስራ መስራት ይጠበቅብናል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ ባገኘናቸው ስኬቶች ሳንዘናጋ የተጀመረው ለውጥ ቀጣይነት እንዲኖረው ሌት ተቀን በትጋት መስራትና የድርሻን መወጣት ይገባል ሲሉም አሳስበዋል።

የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ጃዕፈር ከድር በበኩላቸው፥ የመሀል ዘመን ምንነትን ጨምሮ ወጥመዶች ምንድናቸው፣ ያላቸው እንድምታና እንዴትስ መሻገር ይቻላል እንዲሁም ከማንስ ምን ይጠበቃል የሚሉትን አንኳር ጉዳዮች በዝርዝር አቅርበዋል። የሀገራችንን ሰላምና ለውጡን ለማፅናት ብሎም ዘላቂ ስኬትን ለማረጋገጥ የጠላትን ሴራ ከመከላከል ባሻገር የተገኙ ስኬቶችን ህብረተሰቡ እንዲያውቀው ውጤታማ የሚዲያና ኮሚኒኬሽን ስራ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።

በተጨማሪም የህዝቡን የኑሮ ሁኔታ ማሻሻል፣ ተቋማዊ ሪፎርሞችን ማጠናከርና ቀልጣፋ የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ ስርዓት መዘርጋት እንዲሁም ፍትህን ማረጋገጥ እንደሚገባ ተናግረዋል። በዚህ ረገድ አመራሩና ሠራተኛው ጠንቃቃና ቁርጠኛ በመሆን በመቀናጀትና በመናበብ በጋራ መረባረብ እንዳለበት ገልፀዋል።
