ሚኒስቴሩ ለንግድ ትርዒትና ኮንፈረንሱ መሳካት ላደረገው አስተዋፅዖ እውቅና ተበርክቶለታል

6ተኛው የምስራቅና ደቡባዊ አፍሪካ የጋራ ገበያ ( ኮሜሳ) ሴት ፈጣሪዎች የንግድ ትርዒትና ኮንፍረንስ የመዝጊያ ስነ-ስርዓት በስካይ ላይት ሆቴል ተከናውኗል።

በመዝጊያ ስነ-ስርዓቱ ላይ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ ባስተላለፉት መልእክት፤ የአፍሪካ ነፃ አህጉራዊ የንግድ ቀጠና፣ ለአፍሪካ የንግድ ትስስር የሚኖረውን አስተዋፆ ከፍተኛነት አስታውሰው ሴቶችም በዚህ ቀጠና ውስጥ በስራ ፈጣሪነት፣ በንግድ እና በቢዝነስ የሚኖራቸውን ሚና ለማዳበር ኮሜሳ እያከናወነ ያለውን ተግባር አድንቀዋል። በአህጉራችንም ወጣቶች እና ሴቶች ከዚህ የንግድ ትስስር ከሚኖራቸው ጥቅም ባለፈ ዋና ተዋናይ እና ተጠቃሚ እንዲሆኑ አሁንም የተጠናከረ ስራን እንደሚፈልግም ገልፀዋል። የኢትዮጵያ አገር በቀል የኢኮኖሚቀ ፓሊሲም ከአፍሪካ የንግድ ትስስር ጋር አብሮ በሚሄድ መልኩ እንደተቀረፀ አውስተው በአህጉር ደረጃ የተጠናከሩ ወጣቶች እና ሴቶችን ያማከሉ መድረኮችን መፍጠር ያስፈልጋል ብለዋል።

እንዲህ ዓይነቱ መድረክ በተለይ ወጣት አህጉር ለሆነችው እና በድንበር ዘለል ንግድ ላይ ከሚሳተፉ መካከል 70 በመቶ ሴቶች ለሆኑባት አፍሪካ እጅግ አስፈላጊ ነው ሲሉ ተናግረዋል። ክብርት ሚኒስትሯ አህጉራዊ የፈጠራ ፈንድን በመጀመርና አፍሪካን ከዲጂታል አለም ጋር በፍጥነት እንድትጓዝ በማድረግ ሁሉን አቀፍ እና ጠንካራ ፓን አፍሪካዊ የንግድ ትስስርን እውን ማድረግ እንደሚቻል በአፅንኦት ገልፀዋል። ኮሜሳን ጨምሮ ለንግድ ትርዒትና ኮንፈረንሱ መሳካት አስተዋፆ ያደረጉ አካላትን አመስግነው የንግድ ትርዒትና ባዛሩ በአዲስ አበባ በመከናወኑና እንግዶች የአዲስ አበባን አዲስ ገፅታ ለማየት በመቻላቸው መደሰታቸውን ተናግረዋል።

ሁሌም ኢትዮጵያ በተለመደው መልካም መስተንግዶ እንደምትቀበላቸው ክብርት ሚኒስትሯ ቃል ገብተዋል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን ጨምሮ ለንግድ ትርዒትና ኮንፈረንሱ መሳካት ጉልህ አስተዋፆ ላበረከቱ ተቋማት ምስጋናና እውቅና ተሰጥቷል።

Please follow and like us: