ክብርት ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ከህንድ ልዑካን ጋር በሴቶች የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያዩ

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ በኢትዮጵያ የህንድ አምባሳደር አኒል ኩማር እና ልዑካን ቡድናቸውን ተቀብለው አነጋግረዋል።

የገጠር ሴቶችን አካታች ያደረገ የታዳሽ ሀይል አቅርቦት፣ የሴቶች የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትና በሌሎች የትብብር መስኮች ዙሪያ ከልዑካኑ ጋር ፍሬያማ ውይይት ተካሂዷል።

በውይይቱ ክብርት ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተሰጠውን ሃላፊነት እና በየዘርፉ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን በሰፊው አብራርተዋል።

በገጠር በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሴቶችን በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለማድረግ ያለመ ፕሮጀክት በፓይለት ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ በጋምቤላ ክልል ለመተግበርና በሌሎችም አካባቢዎች ለማስፋፋት መታቀዱን ተናግረዋል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ወደፊትም ሴቶች፣ ወጣቶችና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን ህይወት በተጨባጭ መለወጥ የሚያስችሉ ፕሮጀክቶች ካላቸው አጋር አካላት ጋር ጠንካራ ትብብር ለመፍጠርና በስራ ላይ ለማዋል ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል።

በኢትዮጵያ የህንድ አምባሳደር አኒል ኩማር እና ልዑካን ቡድናቸው በበኩላቸው የታቀደውን ፕሮጀክት ለመደገፍ ፍላጎት እንዳላቸው ገልፀዋል።

በተጨማሪም በህንድ ውስጥ በቴክኖሎጂ የታገዘና፣ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙና በግብርና ዘርፍ የተሰማሩና የብዙዎችን ህይወት በተጨባጭ የለወጠ ተሞክሮ ወደ ኢትዮጵያ ማምጣትና መተግበር እንዲቻል ክብርት ሚኒስትሯ በአካል ተገኝተው እንዲጎበኙ ኦፊሴላዊ ግብዣ አቅርበዋል።

ክብርት ሚኒስትሯ ልዑካኑ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎችን ለመደገፍ ያሳዩትን ተነሳሽነት አድንቀዋል። የህንድ መንግስት በተለያዩ መስኮች ለሚያደርገው ድጋፍና ለልዑካኑ ምስጋና አቅርበዋል።

በቀጣይም የቴክኒክ ኮሚቴ በማቋቋም የቀረበውን የፕሮጀክት ሃሳብ በአጭር ጊዜ ውስጥ በጋራ ለመተግበር የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ለመፈራረም ተስማምተዋል።

Please follow and like us: