የአካል ጉዳተኞችን ሁለንተናዊ ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታትና የተሻለ ተጠቃሚ ለማድረግ በቅንጅት መረባረብ ይጠይቃል – ክብርት ሁሪያ አሊ

ሚኒስቴሩ ከቬንጅ(VNG) ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር 8ተኛውን ብሔራዊ የአካል ጉዳተኞች ተሳትፎ ማስተባበሪያ ፎረም እያካሄደ ይገኛል።

በፎረሙ ከመንግስት አስፈፃሚ አካላት፣ ከአካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን፣ በአካል ጉዳተኞች ዙሪያ ከሚሰሩ አለምና ሀገር አቀፍ ድርጅቶች የተውጣጡ አመራሮችና ተወካዮች ተገኝተዋል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሁሪያ አሊ፥ እንደሀገር የአካል ጉዳቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የተለያዩ የፖሊሲና የህግ ማዕቀፎች እንዲዘጋጁና ተግባራዊ እንዲሆኑ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

የልማት ተደራሽነትና ተካታችነት አጀንዳ የመብት፣ የፍትሃዊነት ጉዳይ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ አካል ጉዳተኞች በየዘርፉ በክብርና በእኩልነት ህይታቸውን መምራት እንዲችሉ ምቹ መደላደል መፍጠር ያስፈልጋል።

በሁለንተናዊ መልኩ የሚገጥሟቸውንም ችግሮች በዘላቂነት ለመቅረፍና የተሻለ ተጠቃሚ ለማድረግ አሁንም በቅንጅት መረባረብ ይጠይቃል ብለዋል።

ለዚህም ሁሉም መንግስታዊ ተቋማት እና የግሉ ሴክተር የአካል ጉዳተኞችን ጉዳይ በሁሉም የልማት እቅዶችና ፕሮግራሞች ውስጥ አካተው ሊተገብሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ብሔራዊ ማህበራት ፌዴሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ አባይነህ ጉጆ በበኩላቸው ባለፉት አመታት የአካል ጉዳተኞች ማህበራትን ለማጠናከር፣ አዳዲስ ማህበራት እንዲፈጠሩ ለማድረግ፣ ከመንግስት ተቋማት ጋር ተቀራርበው እንዲሰሩ ለማስቻል ጥረት መደረጉን ገልፀዋል።

በቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫ፣ በስራ ስምሪት እና በመረጃ ዙሪያ የአካል ጉዳተኞች ተካታችነት ጉዳይ ተገቢው ትኩረት እንዲሰጠው ዋና ዳይሬክተሩ ጠይቀዋል።

መድረኩ የአካል ጉዳተኞችን መብትና ተሳትፎ ለማረጋገጥ የተደረጉ ጥረቶችን ለመገምገም፣ የተገኙ ስኬቶችን ለመዘከር እንዲሁም የሚስተዋሉ ችግሮችን በመለየት መፍትሔዎችን ለማመላከትና ለፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑ ምክረ ሃሳቦችን ለማሰባሰብ ታስቦ መዘጋጀቱን የገለፁት የቬንጅ ኢንተርናሼናል ኢትዮጵያ ተወካይ አቶ ታሪኩ ዋቁማ ናቸው።

በመድረኩ በሀገራዊ ምርጫ፣ በስራ ስምሪት እና በመረጃ ዙሪያ አካል ጉዳተኞችን ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግ የተከናወኑ ተግባራትና ፅሁፎች ቀርበው ውይይት እየተካሄደ ይገኛል።

Please follow and like us: