በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በኢትዮጵያዊነት መንፈስ አገልግላችኋል፤ ህብረተሰቡንም ለበጎ ስራ አነቃቅታችኋል፣ እናከብራችኋለን እንወዳችኋለን፣ እናመሰግናችኋል’ – ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ

የዘንድሮው ወሰን ተሻጋሪ የክረምት የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በስኬት መጠናቀቁ በተዘጋጀው የምስጋና የማጠናቀቂያ መርሐግብር ተገልጿል።

በ‎መርሐግብሩ ላይ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለማህበረሰብ ብሎም ለሀገር ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጥና እድገት ዘላቂነት የጎላ አስተዋፅዖ እያበረከተ መሆኑን ገልፀዋል። በበጎ ፈቃደኝነት አስተሳሰብና መርህ የታነፁ ዜጎችን በመፍጠር፣ ማህበራዊ ግንኙነትንና ትስስርን በማጎልበት፣ ጤናማ አመለካከት እንዲጎለብትና የማህበረሰቡን እሴቶች እንዲቀስሙ ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር ረገድ ውጤቶች እየተመዘገቡ መሆናቸውንም አንስተዋል፡፡ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አገልግሎቱ ተቋማዊ ለማድረግ የሚያስችል ሥርዓት ለመፍጠር በትኩረት እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

በዘንድሮው ወሰን ተሻጋሪ የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ወጣቶቹ የአረንጓዴ አሻራ፣ የደም ልገሳ፣ የአካባቢ ፅዳት፣ የትራፊክ ደህንነት፣ የአቅመ ደካሞች ቤት እድሳት፣ የህሙማን ጥየቃና ድጋፍ፣ የሰላም ግንባታ ላይ ያተኮሩ እና ሌሎችም በጎ ተግባራት ማከናወናቸውን ገልፀዋል። ለዚህም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሀገራዊ እቅድ በማዘጋጀት ከክልሎች ጋር የጋራ መግባባት በመፍጠር ለተግባራዊነቱ ተገቢውን ክትትል ሲያደርግ መቆየቱንና ፕሮግሩሙ በስኬት መጠናቀቁን ጠቅሰዋል ‎’የግል ምቾታችሁን ትታችሁ፣ የህብረተሰቡ ችግር የእኔም ችግር ነው በማለት በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በኢትዮጵያዊነት መንፈስ በቅንነት አገልግላችኋል፤ ህብረተሰቡንም ለበጎ ስራ አነቃቅታችኋል፣ እናከብራችኋለን እንወዳችኋለን፣ እናመሰግናችኋል’ ሲሉ ተናግረዋል።

መርሐግብሩ በስኬት እንዲጠናቀቅም በባለቤትነት ሲሳተፉ፣ ሂደቱን ሲያስተባብሩና በተለያየ መንገድ ድጋፍ ሲያደርጉ የነበሩ አካላት አመስግነዋል። ‎ወጣቶቹ ከወሰን ተሻጋሪ በተጨማሪ በመደበኛው የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ፕሮግራም በንቃት በመሳተፍ ማህበረሰባቸውና አካባቢያቸውን የተሻለ ተጠቃሚ የሚያደርጉ በጎ ስራዎችን እንዲከውኑ ጥሪ አቅርበዋል። የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሙና አህመድ በበኩላቸው፤ ወሰን ተሻጋሪ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች አገልግሎት በየዓመቱ እየጎለበተ መምጣቱን ጠቁመው፤ የ2017 ዓ.ም መርሃ ግብሩ “በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል ሲካሄድ መቆየቱን ተናግረዋል።

‎በጎ ፈቃድ ዘላቂ ሰላም የሚያፀና፣ አብሮነትን የሚያጠናክርና የብዝሃነት መገለጫ መሆኑን አንስተው፤ ወጣቶች በጎነትን የማስረፅ ሚና የተወጡበት መሆኑንም አክለው ገልፀዋል። በስነስርዓቱ ላይ የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ሚኒስቴር ዴኤታን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች ተገኝተዋል ::
‎

Please follow and like us: