Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
የቃሊቲ ሴቶች ማረሚያ ተቋም ውስጥ ለሴት የህግ ታራሚዎች የሚሰጠውን አገልግሎት ለማሻሸል የተገነቡትን ፕሮጀክቶች አስመረቀ፡፡
የቃሊቲ ሴቶች ማረሚያ ተቋም ውስጥ ለሴት የህግ ታራሚዎች የሚሰጠውን አገልግሎት ለማሻሸል የህፃናት የቀን ማቆያና እንክብካቤን ጨምሮ የሥራ ዕድል ፈጠራንና የሙያ ማጎልበቻ ማዕከላትን ጨምሮ ያካተቱ ፕሮጀክቶች አስመርቋል፡፡

በምርቃት ስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) እንደገለጹት ሚኒስቴር መ/ቤቱ የሴቶችንና ህጻናትን መብትና ደህንነት በማስጠበቅ በኩል ያሉትን ህገ መንግስታዊ፣ አህጉራዊና አለም አቀፋዊ ህጎች ተግባራዊ እንዲደረግ ከተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርግ መቆየቱን ገልጸው ከነዚህም ውስጥ ማረሚያ ቤቶች የሴቶችንና ህጻናትን መብትና ደህንነት ባስጠበቀ መልኩ እንዲደራጁ ማድረግ ዋናው መሆኑንም ጠቅሠዋል ፡፡ በተጨማሪም ማዕከሉ በተለይ የህፃናትን መብት ባረጋገጠ መልኩ አገልግሎት አሰጣጡ ከማረሚያ ቤቱ ውጪ በአካባቢው የሚገኙትን ህፃናትንም ጨምሮ በማቆያው እንዲገለገሉ ማድረጉ የማዕከሉን ዓላማ የበለጠ የሚያሣካው መሆኑን ገልፀዋል።

በዚህም የተመረቀው ፕሮጀክት የማረሚያ ተቋማት የእናቶችን ለልጅ እንክብካቤ ያለባቸውን ኃላፊነቶች በብቃት እንዲወጡ አቅምና መነሳሳትን የሚፈጥር መሆኑንም አክለው ጠቅሰዋል፡፡ የፍትህ ሚኒስቴር ክብርት ወ/ሮ ሀና አርዓያስላሴ በበኩላቸው በይፋ የተከፈተው ፕሮጀክት መንግስት በፍትህ ዘርፉ የጀመረውን የለውጥ ጉዞ አይነተኛ ማሳያ ነው ሲሉ ገልጸው መሰል አገልግሎቶችም በሌሎች ማረፈሚያ ቤቶች እንደሚስፋፉ ቃል ገብተዋል፡፡
በተጨማሪም ሚኒስትሮቹ የግንባታውን ስራና ማእከሉን በተለያዩ ቁሳቁሶች በፋይናስና በቴክኒክ ድጋፍ እያደረገ የሚገኘውን የፈረንሳይ ኤምባሲና ሌሎች አጋር አካላትን፣ የማረሚያ ቤቱን የስራ ሃላፊዎች ምስጋናቸውን አቅርበው ለሴቶችና ለህፃናት የሚደረጉ ድጋፎች ከዚህ በበለጠ መልኩ እንዲጠናከሩና በትኩረት እንዲሰራ ሁሉም ባለ ድርሻ አካላት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ አሳስበዋል፡፡
የህፃናትን መብትና ደህንነት አስመልክቶ በአፍሪካ ህፃናት መብትና ደህንነት ቻርተር ላይ እንደተቀመጠው በወላጆቻቸው ሁኔታ ላይ ተመስርቶ አድልዎ ያለማድረግ መብት (አንቀጽ 3)፣ ልጆችን በሚነኩ ተግባራት ላይ ዋነኛ ግምት የሚሰጠው ለልጁ ጥቅምና ስለመሆኑ (አንቀጽ 4(1)፣ በህፃናት ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ማናቸውም የፍትህና አስተዳደራዊ ሂደቶች እንዳይኖሩ (አንቀጽ 4(2)፣ እንዲሁም የህፃናት በሕይወት የመቆየትና የማደግ መብት እንዲጠበቅና የመደመጥ እድል እንደሚሰጣቸው (አንቀጽ 5) ላይ ማስቀመጡ ይታወሣል፡፡
