Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
ፆታ መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች ዙሪያ ግንዛቤ የሚሠጥ አህጉር አቀፍ ውድድር እንደሚካሄድ ተገለፀ
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ(ዶ/ር) የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የሴቶች፣ የሰላም እና ደህንነት ልዩ መልዕክተኛ ጽህፈት ቤት ዋና ኃላፊ የሆኑትን ኦሪያቱ ዳንፋካ በፅ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
በውይይቱ ወቅት ሚኒስትሯ እንደገለፁት፥ ሚ/ር መስሪያ ቤቱ በሴቶች እና ታዳጊ ሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ፆታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶችን ለመከላከል እና ምላሽ ለመስጠት በአገር አቀፍ ደረጃ የፖሊሲ፣ መዋቅራዊ እና የአመለካከት ለውጦች በሚያመጡ ስራዎች ላይ እየሠራ መሆኑን ጠቅሰዋል። በተለይም ከአጋርና ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ፆታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶችን ለማስቀረትና ለመከላከል ብሎም የአመለካከት ለውጥ ለማምጣት የሚረዱ ንቅናቄዎችን በተለያዩ ጊዜያት ማከናወኑን ይህም ውጤት እያመጣ እንደሆነ ጠቁመዋል። ከታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ጋር በመቀናጀት የሴቶች ሩጫን ጨምሮ ከሩጫ የተገኘውንም ገቢ በግጭት ምክንያት ለተጎዱ ሰዎች ተደራሽ ማድረጉን ገልፀዋል።
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የሴቶች፣ የሰላም እና ደህንነት ልዩ መልዕክተኛ ጽህፈት ቤት ዋና ኃላፊ የሆኑት ኦሪያቱ ዳንፋካ በበኩላቸው፥ ሚኒስቴር መ/ቤቱ በንቅናቄ መልክ የአመለካከት ለውጥ ለማምጣት የሚሠራውን ስራ አድንቀው የህብረቱ የሴቶች፣ የሰላም እና ደህንነት ክፍል ፆታ መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች ዙሪያ ግንዛቤ የሚሠጥ አህጉር አቀፍ ውድድር በመዲናዋ ለማድረግ በዝግጅት ላይ መሆኑን ገልፀው ሚኒስቴሩ ለተፈፃሚነቱ ትብብር እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
