Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
የሴቶችና ማህበራዊ ሴክተር የ2018 በጀት ዓመት አንደኛ ሩብ ዓመት አፈፃፀምን ገመገመ
የተጣሉ ግቦችንና የሚጠበቁ ውጤቶችን ለማሳካት የተሰሩ ሥራዎችን የሚያሳይ የሴክተሩ የሩብ ዓመቱ ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ላይ ውይይት ተካሂዷል።
በውይይቱ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) እንደገለፁት፥ ሚኒስቴር መ/ቤቱ ከ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ በመነሳት የዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት በክልሎችና ፌዴራል ከተማ አስተዳደሮች ከሚገኙ መዋቅሮች ጋር በጋራ በመሆን በየሩብ አመቱ ይገመግማል ብለዋል። ባለፉት ሶስት ወራትም በቅንጅት በተሰራው ስራ በዋና ዋና ተግባራት ዙሪያ አመርቂ ውጤት የተመዘገበ መሆኑን ገልፀዋል። በተለይ ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶችና ህፃናት በአንድ ማዕከል አገልግሎት የተጠናከረ ድጋፍ መሰጠቱ፣ በወጣቶች የበጎ ፍቃድ አገልግሎትም የአረንጓዴ አሻራ፣ የአቅመ ደካማ ቤት ጥገና እና ግንባታ፣ የደም ልገሳና የመንገድ ትራፊክ ደህንነት አገልግሎት በስፉት ማከናወን መቻሉ ተጠቁሟል።
መሠረታዊ የማህበራዊ አገልግሎቶችን በማስፋፋት፣ ማህበራዊ ችግሮችን በመከላከል፣ ማህበራዊ ጥበቃ ሥርዓትን በማጠናከር ተጋላጭ ዜጎች ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል ሰፊ ስራ በመስራት ላይ መሆኑን ተናግረዋል።
የሴቶች፣ የህፃናት፣ የአረጋዊያን እና የአካል ጉዳተኞች መብትና ደህንነት ተጠብቆ በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በፖለቲካዊ ዘርፉ የእኩል እድል ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥም እየሠራ እንደሚገኝ ተነስቷል። እንዲሁም ልዩ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ክፍሎች ካሉበት አስከፊ ህይወት እንዲወጡ የማብቃት ስልትን መሠረት በማድረግና በማሸጋገር፣ የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሚያስችሉ ሥራዎችን በማከናወን ላይ መሆኑንም ተናግረዋል።
ውሎና አዳራቸውን ጎዳና ላይ ያደረጉ ዜጎችን ተጠቃሚ ከማድረግ አንፃር በራስ አቅም ከማህበረሰቡ ሀብት በማሰባሰብና ከመንግስት በተገኘ በጀት ከጎዳና ላይ ለማንሳት የተከናወኑ ተግባራት አበረታች መሆናቸውም ተጠቅሷል። አካል ጉዳተኞችን የመሠረታዊ ማህበራዊ ልማት ተጠቃሚ ለማድረግ በተሃድሶ አገልግሎት እየተሰጠ ያለው ተግባር ተጠናክሮ መቀጠሉና ያለባቸው የእንቅስቃሴ ችግር እየተፈታና ተጠቃሚነታቸውም እያደገ መምጣቱ ተገልጿል። በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮች ሳቢያ ለተጎዱ ዜጎች የሚደረገው ድጋፍ፣ እገዛና የበጎ አድራጎትና የማህበረሰብ አገልግሎት ሥራዎች በስፋት የተሰሩበት የዕቅድ አፈፃፀም ወቅት ሲሆን በቀጣይም ተጠናክረው እንደሚከናወኑ በሪፖርቱ ተመላክቷል።
በቀጣይም ያጋጠሙ ችግሮችን በመፍታት የላቀ ውጤት ለማስመዝገብ በሁሉም ዘርፎች በጋራና በቅንጅት መረባረብ ይጠበቅብናል ሲሉ ክብርት ሚኒስትሯ አሳስበዋል። የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ሚኒስቴር ሴቶች፣ ህፃናት፣ ወጣቶች፣ አካል ጉዳተኞች፣ አረጋዊያንና ውሎና አዳራቸውን ጎዳና ላይ ያደረጉ ዜጎችን በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና በፖለቲካዊ መስኮች ያላቸውን ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት ለማሳደግ እንዲሁም የህፃናትን መብትና ደህንነትን ለማስጠበቅ ከአስር ዓመቱ የልማት ዕቅድ የመነጨ የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ በማዘጋጀት ወደ ሥራ መግባቱ ይታወሳል።
