Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
በኢትዮጵያ የቻይና የገጠር ልማት ፋውንዴሽን በማህበራዊ እና በሌሎች መስኮች የጀመረውን የትብብር ስራ እንዲያጠናክር ተጠየቀ
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ የቻይና የገጠር ልማት ፋውንዴሽን ዳይሬክተር ሚስ ይን ሺያንን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በውይይቱ ወቅት እንደገለፁት፥ ፋውንዴሽኑ በኢትዮጵያ ስራ ከጀመረ ጥቂት አመታትን ቢያስቆጥርም አመርቂ ስራዎችን መስራቱን ገልፀዋል። በተለይም በማህበራዊ ጥበቃ፣ የቅድመ ልጅነት እድገት አገልግሎት ማጠናከር፣ ሴቶችን በኢኮኖሚ ማብቃት፣ በትምህርት ቤት ምገባ፣ በፓንዳ ፓክ (የተማሪዎች ቦርሳ) አቅርቦት ላይ ላበረከተው አስተዋፅኦ አመስግነዋል። ሚኒስትሯ እንዳሉት “ፓንዳ ፓክ” በሚል ተቀርፆ ትምህርት ቤቶች ላይ ሲተገበር የቆየውን ፕሮጀክት ለማስቀጠል፣ ለተማሪዎች የሚውሉ ቁሳቁሶችን ከቻይና በብዛት ለማስገባትና መንግስት በዘርፉ የሚሰራቸውን ስራዎች አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል። በተጨማሪም ከገጠር ኮሪደር ልማት ጋር በተያያዘ በተለይም በቻይና ገጠር መንደር ውስጥ “ቦና ቪላ- ቪሌጅ ኮንስትራክሽን” የተሰኘ ፕሮጀክት ተሞክሮ ወደ ኢትዮጵያ ማምጣትና ተግባራዊ ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይም በሰፊው መክረዋል።
በተለይም የኢትዮጵያ የገጠር ኮሪደር ልማት የሚገኙ ሁሉንም ማህበረሰብ ሁሉን አቀፍና እኩል ተጠቃሚ ለማድረግ ያቀደ መሆኑን ጠቁመዋል። የቻይና የገጠር ልማት ፋውንዴሽን ዳይሬክተር ሚስ ይን ሺያን በበኩላቸው፥ ፋውንዴሽኑ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ዜጎችን ለመደገፍ እያከናወናቸውን ያሉትን ተግባራት አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀው ፕሮጀክቶቹ በቀጣይም ከከተማ ባሻገር በሌሎችም የሀገሪቱ አካባቢዎች ለማስፋፋት መታቀዱን ገልፀዋል።
