የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የሀገሪቱን ልማትና እድገት ለማፋጠንና የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የላቀ አስተዋፅዖ ማበርከቱ ተገለጸ

‎የኢ.ፌ.ዴ.ሪ መንግስት የሀገሪቱን ልማትና እድገት በማፋጠን የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ደረጃ በደረጃ ለማረጋገጥ እያደረገ ያለውን ጥረትና ርብርብ በመደገፍ ረገድ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ድርሻው የላቀ እንደሆነ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ ገለፁ።

‎ዘርፉ እንደየአካባቢው ነባራዊ ሁኔታና እንደ ህብረተሰቡ ፍላጎት በተለይ በመንግስትና በህብረተሰቡ ያልተሸፈኑ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ክፍተቶችን ለመሙላት ከፍተኛ እገዛ እያደረገ ይገኛል ብለዋል፡፡ ‎ወጣቶችና ሴቶችን ጨምሮ የተለያዩ አካላትና ተቋማት በየዘርፉ በሚያከናውኗቸው ማናቸውም ጉዳዮች በያገባኛል ስሜት እንዲንቀሳቀሱና በማህበረሰቡ ዘንድ ጠቃሚ እሴቶችን፣ እውቀትና አሰራሮችን እንዲቀስሙ ማስቻሉን ገልፀዋል። ‎በተጨማሪም ወጣቶች የእርስ በርስ ግንኙነታቸውንም እንዲያጠናክሩ፣ ከመንግስት መዋቅር ጋር እንዲቀራረቡና በየአካባቢያቸው እየተሰሩ ያሉ የልማት ስራዎችን እንዲገነዘቡ አድርጓል ብለዋል።

‎‎በአገራቸው ሁለንተናዊ እድገትና የብልጽግና ጉዞ ላይም ደማቅ አሻራቸውን እንዲያሳርፉ ተጨማሪ ዕድል መፍጠር አስችሏል ሲሉ ጠቁመዋል። ‎ሚኒስቴሩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አሰጣጡ በብሔራዊ ደረጃ ወጥነት እንዲኖረውና የታለመለትን ዓላማ እንዲያሳካ ለማስቻል ዘርፉ የሚመራበትን የአሰራር ማዕቀፍ በመቅረጽ፣ ስታንዳርድ በማውጣትና ትግበራውን በማስተባበርና በመከታተል ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
‎

Please follow and like us: