አፍሮ-ማሌዥያ የወጣቶች ፎረም በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡

የአፍሮ-ማሌዥያ የወጣቶች መድረክ የማሌዥያው ጠ/ሚኒስቴር ዳቶ ሴሪ አንዋር ቢን ኢብራሂም እና የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ( ዶ/ር) በተገኙበት በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡

የፎረሙ መክፈቻ ላይ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ( ዶ/ር) ለማሌዥያው ጠ/ሚኒስቴር ዳቶ ሴሪ አንዋር ቢን ኢብራሂም እንኳን ደህና መጡ መልእክት አቅርበው በተጨማሪም የኢትዮጵያ መንግስት ለወጣቶች የሥራ ስምሪት፤ ለወጣቶች ተስማሚ የሆኑ ማህበራዊ አገልግሎቶች እና የስነ-ልቦና ድጋፍ፤ የሲቪክ ተሳትፎ እና የበጎ ፈቃደኝነት ሥራን ማስፋፋት፤ እንዲሁም በፖሊሲ እና በአስተዳደር ውስጥ የወጣቶችን ሁሉን አቀፍ ተሳትፎ ማጠናከር ላይ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

ይህ ፎረምም በዋናነት የማሌዥያን በፈጠራ፣ በአረንጓዴ እድገት፣ በዲጂታል መሠረተ ልማት፣ በትምህርት ጥራት እና በማህበራዊ ጥበቃ ረገድ ያላት እድገት ጠቃሚ ልምዶች ለአፍሪካ ወጣቶች ተጨማሪ አቅም በመሆን እንደሚያገለግል ጠቁመዋል። የአፍሮ-ማሌዥያ የወጣቶች ፎረም አሁን ያለውን ተለዋዋጭ ሁኔታና ፍላጎት በመረዳት እንዲሁም ከዚህ ለውጥ ጋር ሊሄድ የሚችል አዲስ አመራር፣ አዲስ ፈጠራ እና አዲስ ትብብርን በመፍጠር ወጣቶች በዓለም አቀፍ ልማት፣ በዲፕሎማሲ እና ዘላቂ ሰላምና ፀጥታ የራሳቸውን አስተዋጽኦ መፍጠር አለባቸው ሲሉ ጥሪ አስተላልፈዋል፡ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዳቶ ሴሪ አንዋር ቢን ኢብራሂም በበኩላቸው ሰፊ ንግግር ያቀረቡ ሲሆን “ሥልጣኔን ማጠናከር፣ የወደፊት ዕጣ ፈንታን መገንባት፣ የአፍሮ ማሌዥያ አጋርነትን ማጠናከር ለብልጽግና በሚለው ገለጻቸው የአፍሪካ ወጣቶች ከቀደምት ባለ ራዕይ መሪዎቻቸው በመማር የዛሬን ደማቅ የአህጉሪቷን ታሪክ መጻፍ አለባቸው ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስቴሩ እንደገለጹት የአሁኑዋ አፍሪካና ማሌዢያ በአእምሮው ነጻነትን የተጎናጸፈ ወጣት የሚያስፈልግበት ወቅት ላይ መድረሳቸውን ለዚህም እንደአድዋ አይነት ከራሱ አልፎ የሌሎች ጭቆናና የመብት ጥሰቶችን የሚቃወም ሊሆን እንደሚገባ ጠቅሰዋል፡፡ በስነስርአቱ ላይ የአፍሪካ ወጣቶች ፌደሬሽን የኢትዮጵያ ወጣቶች ካውንስል ፕሬዝዳንቶች እንዲሁም ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

Please follow and like us: