Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የስርዓተ-ፆታ ኦዲት ላይ ያዘጋጀውን ማኑዋል በይፋ አስመረቀ
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ከዩኤን ውመን ኢትዮጵያ (UN Women Ethiopia) ጋር በመተባበር ያዘጋጀውን የሥርዓተ-ፆታ ኦዲት ማኑዋል በይፋ አስመርቋል።
ማኑዋሉ በመንግስት ተቋማት ውስጥ በሚከናወኑ የኦዲት ስራዎች ላይ የህዝብ ሀብት በፍትሐዊነት እና ውጤታማ በሆነ መንገድ መተዳደራቸው በተለይም ጾታዊ እኩልነትንና ማህበራዊ አካታችነትን ለማረጋገጥ የሚያግዝ መሆኑ በመድረኩ ተገልጿል፡፡ በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት ዳምጤ መንግስት ለሁሉም ተቋማት በሥራዎቻቸውና በፕሮግሞቻቸው ውስጥ የስርአተ ፆታ እኩልነት አካተው እንዲሰሩ አቅጣጫ ማስቀመጡን አውስተውሰዋል። የፌዴራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤትም የዚህን ተፈጻሚነት በኦዲት ስራዎችን መከታተል ለህዝብና ለመንግስት ተገቢውን መረጃ መስጠት ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑ አብራርተዋል፡፡
ዋና ኦዲተሯ አክለውም የማንዋል ዓላማ በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ውስጥ ሁሉን አቀፍ ኦዲት ለማካሄድ ያለውን የእውቀትና የክህሎት ክፍተት ለመሙላት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ለማኑዋል ዝግጅት ዩኤን ውመን ኢትዮጵያ ላደረገው የቴክኒክ እና የገንዘብ ድጋፍም ላቅ ያለ ምስጋና አቅርበዋል። ማኑዋሉ ለብሔራዊ የልማት ዓላማዎች በኦዲት ውስጥ ያለንን ቁርጠኝነት በተግባር የምናሳይበት ተግባራዊ መሣሪያ መሆኑን በመግለጽ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ኦዲተሮችና አመራሮች “የሥርዓተ-ፆታ ኦዲት ማንዋሉን በላቀ ትጋት” ተግባራዊ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ሚኒስትር ተወካይ አቶ አሳልፈው አመዲን እና የዩኤን ውመን ኢትዮጵያ (UN Women Ethiopia) ሀገራዊ ፕሮግራም ተወካይ ሚስተር ሻድራክ ዱሳቤ በበኩላቸው፥ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን በተለይም ሴቶችን፣ ህጻናትን፣ አካል ጉዳተኞችንና ወጣቶችን አካታችችነት ለማረጋገጥ እያከናወነው ያለውን ተግባራት አድንቀው ለወደፊቱም በመሰል ተግባራት በትብብር እንደሚሰሩ እና ድጋፋቸው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡
በመጨረሻ የተዘጋጀውን የስርዓተ-ጾታ ኦዲት ማኑዋል ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ፣ የዩኤን ዉመን ኢትዮጵያ ተወካይ፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የክዋኔ ኦዲት ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ እና የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳዮች ሚኒስትር ተወካይ በጋራ በመሆን መመረቁን በይፋ አብስረዋል ሲል መ/ቤቱ አስታውቋል፡፡
