Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
ዓለም አቀፉ የጸረ-ሙስና ቀን “ትወልድን በስነ-ምግባር ተቋምን በአሰራር” በሚል መሪ ቃል ተከበረ
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮችና ባለሙያዎች ዓለም አቀፍ የፀረ-ሙስና ቀን በፓናል ውይይት አክብረዋል።
በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የማህበራዊ ዘርፍ አማካሪ ክቡር አቶ ጌታቸው በዳኔ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ ሀገራችን ኢትዮጵያ ከሙስና የጸዳች እና ሁሉንም ዜጋ እኩል ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል ተቋማዊ አደረጃጀት በማቋቋምና ልዩ ልዩ አሰራሮችን በመዘርጋት ስኬታማ እንዲሆን በቁርጠኛነት እየሰራ ይገኛል። አክለውም ሙስና በሀገር እና ህዝቦች ላይ ውድቀት የሚያስከትል አደገኛ ወንጀል መሆኑንም ገልፀዋል። በተለይ ሚኒስቴሩ በሀገሪቱ የሚገኙ ሴቶች፣ ህፃናት፣ አካል ጉዳተኞች፣ አረጋዊያንና ሌሎች ተጋላጭ የማህበረሰብ ክፍሎችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚሰራ ትልቅ ተቋም እንደመሆኑ መጠን የተጣለበትን ሃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት እንቅፋት የሚፈጥሩ ብልሹ አሰራሮችን ለመከላከልና ለማስወገድ በትኩረት መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል።
የሚኒስቴሩ ስራ አመራር ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሙሉጌታ እሸቱ ከሙስና ጋር የተያይዘው ያሉ ጉዳዮች ሀገርን ለማሻገር ትውልድን ለመቅረፅ እና ሀገራችን እየሄደችበት ያለውን የብልፅግና ጉዞ በእጅጉ የሚያደናቅፍ ድርጊት መሆኑን ሙስናን በመቃወምና በመጠቆም ሁሉም ሊረባረብ ይገባል ሲሉ መልእክት አስተላልፈዋል። የስነምግባርና ፀረ-ሙስና ስራ አስፈፃሚ ወ/ሮ ትዕግስት ባይና በበኩላቸው፥ ሙስናን መከላከል ካልተቻለ በሀገሪቱ እየተመዘገበ የሚገኘውን ልማትም ሆነ ሰላምን ማስቀጠል የማይቻል በመሆኑ ሙስናን የሚፀየፍ ጤናማ ማህበረሰብና ትውልድን መፍጠር እንዲሁም ጠንካራ ተቋም መገንባት እንደሚገባና ሁሉም ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት አስገንዝበዋል።
እለቱን በማስመልከት የተቋሙን አገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻል እና የሙስና ተገላጭነት መከላከል በሚቻልበት ጉዳይ ላይ ሰፊ ውይይት ማድረግ ተችሏል።
