ከኮሪያ ዓለም አቀፍ የትብብር ኤጀንሲ (KOICA) ከተ.መ.ድ የስነ-ህዝብ ድርጅት (UNFPA) እና የ.ተ.መ.ድ የስደተኞች ድርጅት ( UNHCR) በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ በጋራ በመተባበር የሚተገበር ከ1.6 ቢሊየን ብር በላይ ወጣቶችና ተጋላጭ ማህበረሰቦችን በዘላቂነት መደገፍ የሚያስችል ፕሮጀክት ይፋ ተደረገ::

ከኮሪያ ዓለም አቀፍ የትብብር ኤጀንሲ (KOICA) እና ከተ.መ.ድ የስነ-ህዝብ ድርጅት (UNFPA) የገንዘብ ድጋፍ የተደረገለትና በ1.6 ቢሊዮን ብር የሚተገበረው ፕሮጀክት በአፋር እና በደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች በግጭት፣ በአየር ንብረት ለውጥ፣ በመፈናቀል እና በማኅበራዊ-ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለተጎዱ ማኅበረሰቦች አጠቃላይ እና ስትራቴጂያዊ ምላሽ ለመስጠት ያለመ ነው።

በማስጀመሪያ ስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) አንደገለፁት ለሦስት ዓመት ተኩል የሚቆየው ይህ ፕሮጀክት በተባበሩት መንግስታት ስነ ህዝብ ፈንድና የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን የሚያስፈፅሙ ሲሆን የክልል ቢሮዎች ደግሞ በመተግበር ፣ ወጣቶችን የማብቃት፣ ቤተሰቦችንና ማኅበረሰቦችን የማጠናከር እና ዘላቂ ሰላምና ልማትን የማረጋገጥ አላማ እንዳለው ገልፀዋል። ፕሮጀክቱ ወደዚህ ምዕራፍ ከመሸጋገሩ በፊት በባለሙያዎች የቅድመ ምዘና ስራ ፣ አሳታፊ ምክክሮች፣ የመስክ ምዘናዎች እና ዝርዝር ሂደቶችን በማለፍ ለዚህ መድረሱን ተናግረዋል። በዚህ ፕሮጀክት ፈጣን የሰብዓዊ ድጋፍ ከማድረስ በዘለል የረጅም ጊዜ የልማት ጣልቃ ገብነቶችን እና የሰላም ግንባታ ጥረቶችን በማዋሃድ ዘላቂና ለውጥ አምጪ ለውጦችን ለማምጣት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ወጣቶች ለልማት ተመልካች ሳይሆኑ ዋና ተዋናዮች፣ ፈጣሪዎች፣ የሰላም ግንባታ ፈጣሪዎችና እና መሪዎች እንዲሆኑ በማስቻልም ረገዱ ሚናው የጎላ እንደሆን ተናግረዋል። ሚኒስቴር መ/ቤቱም ይህንን ፕሮጀክት ተግባራዊ ለማድረግ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት በማስተባበር እንደሚሠራ አረጋግጠዋል። ፕሮጀክቱ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዳሰነች፣ ሰገን ዙሪያና ካራት ዙሪያ የሚተገበር ሲሆን በአፋር ክልል ደግሞ በርሀሌ፣ አብአላ እና አሣይታ ወረዳዎች ፕሮጀክቱ ይፋ ከሆነበት ለሶስት አመት ተኩል ያህል ይተገበራል።

Please follow and like us: