Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
“የተገነባ የወጣቶች ሰብዕና: ሀገር ይገነባል” በሚል መሪ ቃል በወጣቶች ሰብዕና ግንባታ ላይ ያተኮረ የፓናል ውይይት ተካሄደ
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ወጣቶችን በመልካም ስብዕና በማነጽ በአካል፣ በአእምሮ፣ በስነልቦና የዳበሩ ወጣቶችን ለማፍራት የተለያዩ ፖሊሲዎችን፣ ፕሮግራሞችን በመቅረፅ ለተፈፃሚነታቸውም ከሚመለከታቸው ባለድርሻና አጋር አካላት ጋር በመቀናጀት በጋራ እየሰራ እንደሚገኝ የሚኒስቴሩ የወጣቶች ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ ክብርት ሙና አህመድ ተናግረዋል ።
የወጣቶች የስብእና ልማት ማዕከላትን ማስፋፋት እንደ አንድ አጀንዳ በመያዝ ማዕከላቱን ለወጣቶች ተደራሽ ለማድረግ በመላ ሃገሪቱ በርካታ ማዕከላት ተገንብተው ለወጣቶች የእውቀት፣ የክህሎት፣ የስራ ፈጠራና የመዝናኛ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ እነዚህን ማዕከላትም ወደ ሶሻል ኢንተርፕራይዝ የማሳደግ ስራና የወጣቶች ስብዕና ልማት 5 አመት ስትራቴጂ በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል። መንግስት የወጣቶች ስብዕና ግንባታ ላይ ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴዎች እያከናወነ ቢሆንም ጥረት እንዳለ ሆኖ በዘመናት ውስጥ የሚፈጠሩ ዓለም ዓቀፋዊ ቀውሶች በትውልዱ ብሎም በማህበረሰቡ ላይ አሉታዊ
ተፅዕኖ የሚያሳርፉ አደንዛዥ ዕፆች እና አሉታዊ መጤ ልማዳዊ ድርጊቶች የወጣቱ ትልቅ ፈተና መሆናቸውን ገልፀዋል።
ይህንን ችግር ለመከላከልና ምላሽ ለመስጠት በቅንጅትና በትብብር መስራት እንደሚገባ ጠቅሰው ኃላፊነቱን የአንድ ተቋም ወይም የጥቂት ግለሰቦችና ቡድኖች ጉዳይ ተደርጎ መወሰድ እንደሌለበት አፅዕኖት በመስጠት ተናግረዋል ። ስለሆነም የወጣቶችንና ታዳጊዎችን ስብዕና በመገንባት በራሳቸው ባህልና ታሪክ የሚኮሩ፣ በስነ-ምግባር የታነፁና ሃገራቸውን የሚወዱ፣ ጤናማና አምራች ዜጋ እንዲሆኑ ሁሉም የበኩሉን አስተዋፅኦ እንዲያበረክት ጥሪ አቅርበዋል።
በዕለቱ በተካሄደው የፓናል ውይይትም ቤተሰብ፣ የእምነት ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶች፣ የሚዲያ አካላት፣ የጉዳዩ ባለቤት የሆኑ ወጣቶች አና ወጣት ማህበራት የወጣቶችን ስብዕና ከመገንባት አንፃር እንደ ሀገር እየተሠሩ ያሉ ስራዎችንና የመፍትሄ አቅጣጫዎችን አመላክተዋል።
