Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙና ልዩ ድጋፍ ለሚሹ 300 ተማሪዎችና ወላጆች ድጋፍ ተደረገ
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር በኢትዮጵያ ከቻይና የገጠር ልማት ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር በልደታ ክፍለ ከተማ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙና ልዩ ድጋፍ ለሚሹ 300 ተማሪዎችና ወላጆች ለእያንዳንዱ አምስት ሊትር የምግብ ዘይትና አስር ኪሎ 1ኛ ደረጃ ዱቄት ድጋፍ አድርጓል።
በድጋፍ ርክክብ በመርሐ – ግብሩ ላይ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ሚኒስቴሩ ባለድርሻና አጋር አካላትን በማስተባበር ያሉትን ማህበራዊ ችግሮች ለማቃለል ከዚህ ቀደም ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰዋል። ችግሮችን በዘላቂነት ለመቅረፍ ከሚደረጉ ጥረቶች ጎን ለጎን አቅም በፈቀደ መጠን የሚስተዋለውን ችግር ጊዜያዊ መፍትሔ ማበጀት ተገቢ በመሆኑ ድጋፉ ወደፊትም ቀጣይነት እንደሚኖረው ተናግረዋል። ፋውንዴሽኑ በተለያዩ ጊዜያት እያበረከተ ላለው አስተዋፅዖም በተጠቃሚዎች ስም አመስግነዋል።
በኢትዮጵያ የቻይና የገጠር ልማት ፋውንዴሽን ይን ሺያን ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር ትብብርን በማጠናከር የአጭርና የረጅም ጊዜ እቅድ በመንደፍ በተለያዩ መስኮች የሚያደርገውን ሁለንተናዊ ድጋፎች አንደሚቀጥል ተናግረዋል። የክፍለ ከተማው ዋና ስራ አስፈፃሚ ወ/ሮ ልዕልቲ ግደይ በበኩላቸው በክፍለ ከተማው አነስተኛ ገቢ ያላቸውን የህብረተሰብ ለመድረስ ሰው ተኮር ፕሮግራም ተቀርፆ እየተተገበረ መሆኑን ገልፀው ሚኒስቴሩ ከፋውንዴሽኑ ጋር በመሆን ላድረገው ድጋም ምስጋና አቅርበዋል።
