‎በሰብል ልማት፣ በእንስሳት እርባታና በሌሎችም መስኮች ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ያሉ ስራዎች የሚያበረታቱና የአመራሩን ቁርጠኝነት የሚያሳዩ መሆኑን መመልከት ችለናል – ክብርት ሙና አህመድ

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በስልጤ ዞን የወጣቶችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለማሳደጎ የተከናወኑ ተግባራት ላይ የክትትልና ድጋፍ ስራ ተካሂዷል።

‎በጉብኝቱ የተሳተፉት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሙና አህመድ ከተቋሙ የክትትልና ድጋፍ ቡድን አባላትና ከክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ጋር በመሆን በስልጤ ዞን አልቾ ውሪሮ ወረዳ ገጀራት ቀበሌ በስንዴና ገብስ ምርት ማምረት ዘርፍ የተሰማሩ ወጣቶችን የስራ እንቅስቃሴ ተዟዙረው ተመልክተዋል። ‎እንዲሁም የክትትልና ድጋፍ ቡድኑ በወራቤ ከተማ አስተዳደር በዶሮ እርባታና በንብ ቀፎ ማምረት ተግባር የተሰማሩ ወጣቶች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን ጎብኝቷል። ‎ጉብኝቱን ተከትሎም የወጣቶች ጉዳይ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሙና አህመድ እንዳሉት ለስራ አጥ ወጣቶች ሰፋፊ መሬቶችን በመስጠት በስንዴ እና ገበስ ምርት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያደረገበት መንገድ የሚደነቅና የአመራሩን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑን ተናግረዋል

‎በቀጣይም በስራ እድል ፈጠራና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ከመስጠት ጎን ለጎን በአካባቢው ያሉ ፀጋዎችን በመለየት፣ ክትትልና ቀጣይነት ያለው ድጋፍ በማድረግ ወጣቶች የራሳቸውን ስራ እንዲፈጥሩና ውጤታማ እንዲሆኑ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል። ‎የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ም/ቢሮ ሃላፊ አቶ ሱልጣን በበኩላቸው ለወጣቶች የስራ እድል ግንዛቤ ከመፍጠር በተጨማሪ የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከሌሎች ተቋማት ጋር ቅንጅት በመፍጠር በጋራ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል። ተግባሩ ወደፊትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል።

በሌላ በኩል በወራቤ ከተማ በተገነባው የወጣት ማዕከል እየተሰጠ ያለውን አገልግሎት አስመልክቶ የክትትልና ድጋፍ ቡድኑ ጉብኝት ያደረገ ሲሆን አጠቃላይ በክልሉ በተካሄደው ምልከታ በታዩ ጠንካራ፣ ጎኖች፣ ክፍተቶችና ቀጣይ ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች ዙሪያ የሚመለከታቸው አስፈፃሚ አካላት በተገኙበት ግብረ-መልስ ተሰቷል።

Please follow and like us: