‎በሰውነታችን ተከባብረን በሰላም የምንኖርባት፣ ህብረ ብሔራዊ አንድነቷ የተጠበቀ እና የበለፀገች ኢትዮጵያን ለመገንባት ሁላችንም ኃላፊነታችንን እንወጣ

“እኔ በሰውነቴ ከማንም አልበልጥም፤ አላንስም! እርስዎስ?” በሚል መሪ ሃሳብ በሰላም እሴት ግንባታ ላይ ያተኮረ ሀገር አቀፍ ምክክር ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ያለመ ውይይት ተካሄደ።

‎‎በውይይቱ የሚኒስቴሩ ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ ከሃይማኖት ተቋማት፣ ከፌዴራል ሴክተር መስሪያ ቤቶች፣ ከሴትና የወጣት አደረጃጀቶች እንዲሁም ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የተውጣጡ ተወካዮች ተሳትፈዋል። ‎የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ በዚሁ ጊዜ፥ ዜጎች በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ረገድ ያላቸውን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ብሎም በየአቅጣጫው – በየዘርፉ የተወጠኑ ሀገራዊ የልማት ግቦችን ለማሳካት ሰላም ወሳኝ ሚና አለው ሲሉ ገልጸዋል። ‎ሰላም ሲታጣ ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል ተጎጂ መሆኑን በተለይም ደግሞ ሴቶች፣ ህፃናት፣ ወጣቶች፣ አካል ጉዳተኞች እና አረጋውያንን ግንባር ቀደም ተጎጂ እንደሚያደርግና የበረታ ጫናም እንደሚያሳድር ተናግረዋል።

‎‎የሰላም ጉዳይ ሁሉንም የሚመለከት እንደመሆኑ በሰላም ዙሪያ በጋራ መቆም ያስፈልጋል ያሉት ክብርት ሚኒስትሯ፥ ሰላምን ማፅናት የሚያስችል የጋራ አስተሳሰብ ማዳበር፣ መተሳሰብንና መከባበርን መሠረት ያደረገ ማህበረሰብ መፍጠር እንደሚገባ ገልፀዋል። ‎በመሆኑንም ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል አካታች ባደረገ መልኩ ምክክር የሚካሄድበት ምቹ መደላደል በመፍጠር ሁሉም ለሰላም ዘብ እንዲቆሙና በባለቤነትት እንዲረባረቡ በቅንጅት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።

‎በሰውነታችን ተከባብረን በሰላም የምንኖርባት፣ ‎ህብረ ብሔራዊ አንድነቷ የተጠበቀ እና የበለፀገች ኢትዮጵያን ለመገንባት የሚያስችል ገዢና አሰባሳቢ ሃሳብ በመሆኑ ሁላችንም ኃላፊነታችንን እንወጣ ሲሉ ክብርት ሚኒስትሯ ተናግረዋል።

Please follow and like us: