Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
ባህላዊ ፍርድ ቤቶች እንዲጠናከሩ የክልሉ መንግሥት ይሰራል፡- የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ
ባህላዊ ፍርድ ቤቶች አማራጭ የፍትሕ መስጫ ሥርዓት በመሆናቸው እንዲጠናከሩ እና ማህበራዊ ፍትሕ እንዲሰፍን የክልሉ መንግሥት እንደሚሰራ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ ተናግረዋል።
የአማራ ክልል የባህል ፍርድ ቤቶች እውቅና መስጫ እና ሥራ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር በባሕርዳር ከተማ ተካሂዷል። የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ በዚህ ወቅት እንደገለጹት፤ ባህላዊ ፍርድ ቤቶች ቂምንና ጥላቻን በመሻር ማህበራዊ ፍትሕን በማንገስ ረገድ ትልቅ ሚና አላቸው። ባህላዊ ፍርድ ቤቶች ለሕግ የበላይነትና ለፍትሕ መስፈን አዎንታዊ ሚና አላቸው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ እንደ ክልል የገጠመንን ችግር ለመፍታት አይነተኛ መሳሪያ ነው ሲሉ ነው የተናገሩት፡፡

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ በበኩላቸው፤ ባሕላዊ ፍርድ ቤቶች ለህፃናት፣ ለአካል ጉዳተኞች፣ ለሴቶች እና ለሌሎች ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎች አዎንታዊ ሚና እንዳላቸው ጠቅሰዋል:: ባህላዊ ፍርድ ቤቶች ግጭቶችን ከመፍታት እና ከፍትሕ አገልግሎት ባሻገር ለማህበረሰቡ ሁለንተናዊ መስተጋብር ያላቸው ሚና የጎላ በመሆኑ በትኩረት ሊሠራባቸው እንደሚገባም አስገንዝበዋል። ሚኒስትሯ የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመደበኛ ፍርድ ቤቶች የሚሰጡት አገልግሎቶችን የሚያግዙ እና የፍርድ ቤቶችን ጫና የሚቀንሱ የባህላዊ ዳኝነት ስርዓትን ለማጠናከር እየሰራ ያለውን ስራ አድንቀዋል። ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ አበረታችና ውጤታማ የሪፎርም ስራዎችን እያከከናወነ መሆኑን በጉብኝቱ ወቅት መመልከት መቻሉንም ገልፀዋል፡፡ በባህላዊ ፍርድ ቤት እየሰሩ ያሉ አካላት ሰላምን የማጽናት እና ማህበረሰባዊ መስተጋብርን የማጠናከር ስራን በተሻለ ሁኔታ አጠናክረው እንዲቀጥሉ አደራ ብለዋል።
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ዓለምአንተ አግደው በበኩላቸው፤ ባህላዊ ፍርድ ቤቶች ከግለሰብ ጀምሮ ግጭቶችን በሠላማዊ መንገድ ለመፍታት ትልቅ ሚና አላቸው ብለዋል።
ዘርፉን የተሻለና ውጤታማ ለማድረግ ከለውጡ በኋላ እንደ ሃገር በተጀመሩ የፍትሕ ሪፎርም ሥራዎች፣ ባህላዊ ፍርድ ቤቶችን በመጠቀም የፍትሕ ሥርዓቱን ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። በመርሐ ግብሩም በክልል በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በጥናት የተለዩ 15 አማራጭ ያለመግባባት መፍቻ ዘዴዎች እውቅና ተሰጧቸዋል ሲል ኢቢሲ ዘግቧል።
