Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
በየዘርፉ የሚስተዋሉትን ችግሮችን እየፈታን ማህበረሰባችንን የተሻለ ተጠቃሚ የሚያደርግና ኢትዮጵያንም ወደ ፊት የሚያሻግር ስራ መስራት እንደሚጠበቅ ተገለፀ
የሴክተሩ የ2018 በጀት አመት የ6ወር እቅድ አፈፃፀም ጠንካራና ደካማ ጎኖችን በመፈተሽ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ አንኳር ጉዳዮችን በመለየት የቀጣይ አቅጣጫ አስቀምጧል።
በጉባኤ ማጠቃለያ ላይ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ፥ ባለፋት 6 ወራት የዜጎችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አኳያ በየዘርፉ ሊቆጠሩ የሚችሉ በርካታ ውጤታማ ስራዎች መሰራታቸውን ገልፀዋል። ቅንጅታዊ ስራዎች፣ የክትትልና ድጋፍ ተግባራት እና የግብረ መልስ አሰጣጥ አሰራር እየተጠናከረ መምጣቱ ለተገኘው ውጤት አስተዋፅዖ ማበረከቱን ተናግረዋል። የተገኘው ስኬት በየደረጃው የሚገኙ አስፈፃሚ አካላት ድምር ውጤት መሆኑንም በመግለፅ በአግባቡ ሲመሩና ሲደግፉና ለቆዩ የልማት አጋሮችም ምስጋና አቅርበዋል። በቀጣይም ተጋላጭ ዜጎችን በዘላቂነት በመደገፍና ከተረጂነት በማላቀቅ ወደ አምራችነት እንዲሸጋገሩ ለማስቻል የማህበረሰብ ተሳትፎንና ጥምረቶችን ማጠናከር ይገባል ብለዋል።
የቤተሰብ ተቋም እና የማህበረሰብ ድጋፍና ክብካቤ ጥምረቶችን ላይ መስራት በርካታ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመፍታት ያስችላል ያሉት ክብርት ሚኒስትሯ ያሉትን ማህበራዊ አቅሞቻችንን በደንብ መጠቀም ይገባል ብለዋል። የስራ ባህል ከተቀየረ ወጣቶችን ተጠቃሚ ማድረግም ሆነ የሀገራችንንም ብልፅግና ማረጋገጥ ይቻላል፤ በመሆኑም የስራ ባህልን የበለጠ ለማሻሻል እንዲሁም ያልተቋረጠ የስብዕና ግንባታ ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት ያስፈልጋል ሲሉ ገልፀዋል። የቀዳማይ ልጅነት የትምህርትና እድገት ክብካቤ ፕሮግራም እና የህፃናት ጉዳይ መረጃ አያያዝ አስተዳደር ስርዓትን ለማጠናከርና ውጤታማ ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎችን አልቆ ማስቀጠል እንደሚገባ ጠቁመዋል። ሰላም የሁሉም መሠረት በመሆኑ የሰላም ግንባታ ላይ የሴቶችና የወጣቶችን ሚና ለማሳደግ የተጀመሩ ጥረቶች መጠናከር እንዳለባቸው ገልፀዋል።
ዲጂታላይዜሽንን በተመለከተ አገልግሎትን ማዘመንና የ5ሚሊዮን ኮደርስ ኢኒሼቲቭ እንዳሳካ ብሎም ሀገራዊ ምክክሩ እንዲሰምር እና መጪው ሀገራዊ ምርጫም ግልፅ፣ ፍትሐዊና ተአማኒ እንዲሆን በቅንጅት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል። ሌሎች ሀገራዊ አቅጣጫዎችንም ከተቋማዊ ግቦች ጋር ማስተሳሰርና በትኩረት መፈፀም እንደሚገባ ተናግረዋል። በየዘርፉ የሚስተዋሉትን ችግሮችን እየፈታን ማህበረሰባችንን የተሻለ ተጠቃሚ የሚያደርግና ኢትዮጵያን ወደ ፊት የሚያሻግር ወጤት ለማስመዝገብ በትጋት መስራት ይጠበቅብናል ሲሉ አሳስበዋል።
