Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
ክብርት ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ አዲስ ከተሾሙት የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ምክትል ሊቀመንበር ማዳም ሰሊማ ማሊክ ጋር አጋርነትንና ትብብርን ማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ተወያዩ
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ አዲስ ከተሾሙት የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ምክትል ሊቀመንበር ማዳም ሰሊማ ማሊክ ጋር አጋርነትንና ትብብርን ማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ፍሬያማ ውይይት አካሄዱ።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ለማዳም ሰለማ መልካም የስራ ዘመን እንዲሆን ተመኝተዋል፤ ለኢትዮጵያ የሚያደርጉት ደጋፍ እንደሚቀጥልም ያላቸውን እምነት ገልፀዋል። የኢትዮጵያ መንግስት ጠንካራ የማህበራዊ ጥበቃ ስርዓት በመዘርጋት የዜጎችን ህይወት ለማሻሻል በርካታ ስራዎች እያከናወነ መሆኑን ገልፀው በዚህ ረገድ የአፍሪካ ሕብረት እያደረገ ላለው ጠንካራ ትብብርና አጋርነት ከፍ ያለ ምስጋና አቅርበዋል። የስራ ኋላፊዎቹ ሀገር በቀል እውቀቶችና እሴቶችን ለአህጉሪቱ ችግሮች መፍቻነት በማዋል የምንመኛትን አፍሪካ እውን ከማድረግ አንፃር ጉልህ አስተዋፅዖ ያለውና በአህጉር ደረጃ ፖሊሲ አውጪዎችና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የሚሳተፉበት የማህበራዊ ጥበቃ ኮንፈረንስ በጋራ ማዘጋጀት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ በሰፊው መክረዋል። እንዲሁም የሴቶችና የወጣቶች የሰላምና ደህንነት የድርጊት መርሐግብርን ከአጀንዳ 2063 እና ከUNSCR 1325 ጋር በማስተሳስር መተግበር አስፈላጊ መሆን ጠቁመው ህብረቱ ለዝግጅቱ ጠንካራ የቴክኒክ ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።
የኢትዮ-ኢንተርናሽናል የተማሪዎች የውድድር ፌስቲቫል መካሄዱ በተማሪዎች መካከል ለሳይንስና ፈጠራ ያለውን ምልከታና ተነሳሽነት የሚያሳድግ በመሆኑ አስፈላጊውን እገዛ እንደሚደረግ ተገልጿል። ውይይቱን ተከትሎ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ምክትል ሊቀመንበር ማዳም ሰሊማ ማሊክ፣ የኢትዮጵያ መንግስት እየሰራ ያለውን የልማት ስራዎች አድንቀዋል። የቀረፁት ኢኒሼቲቮች ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ያለውን ትብብርና አጋርነት የበለጠ የሚያጠናክር መሆኑን ገልፀው በቀጣይም በጋራ ለመስራት ፍላጎት እንዳለና የተጀመረው ድጋፍም የበለጠ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
