ክብርት ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ በኢትዮጵያ የቱርክዬ አምባሳደር ሚስተር በረክ ባራን ጋር በሁለትዮሽ ጉዳይ ዙሪያ ውጤታማ ውይይት አደረጉ

‎የኢፌዴሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ በኢትዮጵያ የቱርክዬ አምባሳደር ሚስተር በረክ ባራን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

‎ውይይቱ በዋነኝነት የአፍሪካ – ኤዥያ የወጣቶች ፎረምን በጋራ ለማዘጋጀት፣ የሴቶች ንፅህና መጠበቂያ ፓድ ምርትና ስርጭት፣ የአካል ጉዳተኞች አጋዥ ቁሳቁስ ተደራሽነት፣ በወጣቶችና ሴቶች አመራርነት አቅም ማሳደግ እንዲሁም በእደ ጥበብ የተሰማሩ ሴቶችን ተጠቃሚነት ማጎልበት ላይ ትኩረቱን ያደረገ ነበር። ክብርት ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ በውይይቱ ጊዜ፥ ሁለቱ ሀገራት በመከባበርና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሠረተ ረጅም ጊዜን ያስቆጠረ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዳላቸው፣ በተለያዩ መስኮችም ጠንካራ ትብብር እያደረጉና የጋራ ግቦችን ለማሳካት በጋራ እየሰሩ እንደሆነም ገልፀዋል።

‎‎ቱርኪዬ በኢትዮጵያ የሴቶች ንፅህና መጠበቂያ ፓድ ምርትና ድጋፍ፣ ለአየነ ስውራን የሚውል የቤተ-መፅሐፍት ግንባታ፣ የአካል ድጋፍ ተደራሽነትን ለማሳደግ እያደረገች ላለው አስተዋፅዖ ምስጋና አቅርበዋል። በኢትዮጵያ የቱርክዬ አምባሳደር ሚስተር በረክ ባራን በበኩላቸው፥ በሀገራቱ መካከል በብዙ መስኮች ጥብቅ ትስስር ያለ መሆኑንና ይህንኑ የበለጠ የሚያጠናክሩ ተግባራት እንደሚከናወኑ ተናግረዋል።

‎ቱርኪዬ የተጀመሩ ስራዎችን ወደፊትም አጠናክራ እንደምትቀጥል አስታውቀዋል። ውይይቱ ባተኮረባቸው የትብብር መስኮችም ቱርኪዬ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደምታደርግ ክቡር አምባሳደር በረክ ገልፀዋል።
‎

Please follow and like us: