Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
5ኛው ዙር የኢትዮጵያ የስነ-ህዝብና ጤና ዳሰሳ (DHS) ጥናት ውጤቱ ክፍተቶችን በመሙላትና ስኬታማ አፈፃፀሞችን በማጠናከር የቀጣይ ስራዎችን ውጤታማ ለማድረግ መሠረት ሆኖ ያገለግላል- ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ
የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ያካሄደው 5ኛው ዙር የስነ-ህዝብ እና ጤና ዳሰሳ (DHS) ጥናት የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት ውጤት ለተጠቃሚዎች ይፏ ሆኗል፤ በጥናቱ ቁልፍ አመላካች ውጤቶች ዙሪያም ባለድርሻ አካላት ውይይት እያካሄዱ ይገኛል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ በዚሁ ጊዜ፥ ሚኒስቴሩ ሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች፣ አረጋውያንና አካል ጉዳተኞችን ጨምሮ ለችግር ተጋላጭ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎችን ችግሮች ደረጃ በደረጃ ለመፍታት እና ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ያለሙ ሰፋፊ ተግባራትን በቅንጅት እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል። የጥናት ውጤቱም ክፍተቶችን በመሙላትና ስኬታማ አፈፃፀሞችን አጠናክሮ በማስቀጠል በቀጣይ የማህበራዊ ፕሮግራሞችን የበለጠ ውጤታማ ለማድረግና የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መሠረት ሆኖ ያገለግላል ብለዋል ።
በተጨማሪም ከቁጥር በዘለለ የጥናት ውጤቱ የተለያዩ ፖሊሲዎችን፣ ስትራቴጂዎችንና ፕሮግራሞችን ለመንደፍና ለመተግበር ከፍተኛ እገዛ እንደሚያደርግ ተናግረዋል። 5ኛው የDHS ውጤት ባለፉት ስምንት ዓመታት ስኬትና ለውጥ ያመጡ ጥረቶችን የሚያሳይ ቢሆንም፤ የላቀ ውጤት ለማስመዝገብ መፍጠን እንደሚገባ አመላካች መሆኑን ገልፀዋል። የተገኘው ውጤት የሚያስደስት ቢሆንም፣ አሁንም ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች በመኖራቸው በሴክተር እቅድ ውስጥ በማካተት ምላሽ መስጠት ይገባል፤ ለዚህም የተቀናጀ ጥረት ከሁላችንም ይጠበቃል ብለዋል።
ሚኒስቴሩ በተለይ ሴቶችን ከማብቃት፣ ጾታን መሠረት ካደረጉ ጥቃቶች፣ ከጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች እና ሌሎችም ትኩረት ተሰጥቷቸው በጥናቱ የተካተቱ ቁልፍ አመላካቾችን መነሻ ያደረጉ ውጤታማ ተግባራትን ለማከናወን ከባለድርሻና አጋር አካላት ጋር በቅንጅት ይሰራል ብለዋል። የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ስርዓተ ጾታን ማዕከል ባደረገ፣ በተቀናጀና አካታች በሆነ አግባብ ጥናቱ እንዲካሄድ እና ይፋ እንዲሆን ላሳየው የአመራር ቁርጠኝነት ምስጋና አቅርበዋል።
