‎”አፍሪካና ህንድ በሰው ኃይል ልማትና በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ያላቸውን አጋርነት ያጠናክራሉ” — ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)

“በአፍሪካ ሕብረት የልማት ኤጀንሲ (AUDA-NEPAD) እና ማሕበራዊ እና የልማት ለውጥ ማዕከል (CSEP) አማካኝነት የተዘጋጀ የአፍሪካ ሕንድ የልማት አመላካች የጥናት ውጤት ይፋ ሆኗል።

‎የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ እንደገለፁት፥ የአፍሪካን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መዋቅር ለመቀየር የሰው ኃይል ልማት ስላለው ሰፊ ሚና እንደሚኖረው ጠቅሰዋል። የህንድና አፍሪካ ግንኙነት ከንግድ ባለፈ “በሰው ተኮር” ልማት ላይ በማተኮር ለወጣቶችና ሴቶች የክህሎት ዕድል፥ አፍሪካ ያላትን እጅግ ከፍተኛ የወጣት ኃይል ወደ ምርታማነት ለመቀየር የህንድ የቴክኒክና ሙያ (STEM) ልምድ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰዋል። በተለይም ሴቶች በዲጂታል ኢኮኖሚው ውስጥ ንቁ ተሳትፎ እንዲኖራቸው የሚያስችሉ ስልጠናዎች በትብብሩ መካተታቸውን አድንቀዋል።  ‎በማህበራዊ ጥበቃና የዲጂታል ቴክኖሎጂ መሠረተ ልማት ተሞክሮን በመጠቀም፣ የማህበራዊ ድጋፍ ለሚሹ ዜጎች ቀልጣፋና ግልጽነት ያለው የፋይናንስ ተደራሽነት (Fintech) መፍጠር እንደሚቻል ገልጸዋል።

‎‎”ይፋ የተደረገው ጥናት የፋይናንስ ግኝት እድሎችን ለማሳደግ፣ የኢንቨስትመንት አማራጮችን ለማስፋት እና አጋርነትን ለማሳደግ ወሳኝ ነው ያሉት ሚኒስትሯ፣ ይህም ከአህጉሪቱ “አጀንዳ 2063” ራዕይ ጋር የተጣጣመ መሆኑን አስረድተዋል። ‎የህንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ የኢትዮጵያ ጉብኝት የሀገራቱን ግንኙነት ወደስልታዊ አጋርነት ከፍ ያደረገ መሆኑን አንስተው የደቡብ ደቡብ ሀገራትን የአቻነት ትብብርን ያሳየ መሆኑን ተናግረዋል።
‎

‎በኢትዮጵያ የህንድ አምባሳደር አኒል ኩማር ራይ በበኩላቸው፣ ህንድ ለአፍሪካ የኢንዱስትሪ ሽግግር ያላትን ቁርጠኝነት ገልፀው አፍሪካ የሚገኙ እንደ ሊቲየም ያሉ ወሳኝ ማዕድናትን ለማልማት ያቀደችው ኢንቨስትመንት፣ አህጉሪቱ የጥሬ ዕቃ ላኪነት ታሪኳን ቀይራ የራሷን የባትሪና የኤሌክትሮኒክስ ፋብሪካዎች እንድትገነባ የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል። በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ፣ ይህ የትብብር ማዕቀፍ በአፍሪካና በህንድ መካከል ያለውን ታሪካዊ ግንኙነት ወደ ተጨባጭ የኢኮኖሚ ውጤት የሚቀይር መሆኑ ተመላክቷል። ትብብሩ በዋናነት አካታች ዕድገት፣ አረንጓዴ ኢነርጂ እና ዲጂታል ትራንስፎርሜሽንን መሠረት በማድረግ ለሁለቱ ወገኖች የጋራ ብልጽግናን ያረጋግጣል ተብሏል።
‎

Please follow and like us: