Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
ከትዳር በፊት የቅድመ ጋብቻ ስልጠናን አስመልክቶ የተሰጠ መግለጫ
ጋብቻ ተቻችሎና ተከባብሮ አብሮ መኖርን የሚጠይቅ ረጅም የህይወት ጉዞ ነው። ትዳር ቤተሠብ የሚመሰረትበት፣ ትውልድ የሚገነባበት የህብረተሰብ መሰረትና ትልቅ ማህበራዊ ተቋም እንደሆነ ይታመናል። ስለሆነም ጋብቻ ለጠንካራ ቤተሰብ ምስረታና ለሀገር ግንባታ መሠረት እንዲሆን ተደርጎ መፈፀም ይኖርበታል።
ሆኖም ስለትዳርም ሆነ ስለቤተሰብ ምስረታ ባለው ዝቅተኛ ግንዛቤና በሌሎችም ምክንያቶች ሳቢያ ፍቺ ሲከሰት ይስተዋላል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚንስቴር “ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የፍቺ ቁጥር ለመቀነስ፣ የቅድመ ጋብቻ ስልጠና ሰርተፊኬት ሳይዝ ማንም ሰው ወደ ጋብቻ እንዳይገባ የሚያደርግ አሰራር ሊጀምር ነው” በሚል በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያዎች እየተሰራጨ ያለው ዘገባ የተሳሳተ መሆኑን እንገልጻለን።
ሚኒስቴሩ ጥንዶች ስለሚጀምሩት አዲስ የሕይወት ምዕራፍ በቂ ዕውቀት እንዲኖራቸውና ጠንካራ ቤተሠብ መመስረት እንዲችሉ ለማድረግ የቅድመ ጋብቻ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መስጠት አስፈላጊ መሆኑን በውል ይገነዘባል።
ይህ በተለያዩ ሀገራትም እንደ አንድ መፍትሔ ተደርጎ እየተሰራበት እና በሀገራችንም አንዳንድ የሃይማኖት ተቋማት በዚህ ላይ እየሰሩበት እንደሚገኙ ይታወቃል።
ይሁን እንጂ ሚኒስቴሩ ይህን “ከሚቀጥለው አመት ጀምሮ አስገዳጅ ለማድረግ ያለመ የአሰራር ማዕቀፍ እያዘጋጀ ነው” የሚለው ፍፁም የተሳሳተ መረጃ በመሆኑ ሊታረም ይገባል።
ጥንዶች ስልጠና መውሰድ የሚችሉበትን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ሚኒስቴሩ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ ይቀጥላል። ከስልጠና በተጨማሪ ትዳር እንዳይናጋና ቤተሠብም እንዳይበተን ቤተሠብ ተኮር የምክር አገልግሎቶችን ለማስፋፋት እና ለማጠናከርም በትኩረት እየሰራ ይገኛል።
በቤተሰብ ጉዳይ ላይ የሚሰሩ ተቋማት ሥራቸውን ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችል የጋራ ፎረም ተመስርቶ ወደ ተግባር እ
ተገብቷል።
እንደአጠቃላይ ፍቺን ለመቀነስም ሆነ ቤተሠብን ለማፅናትና የሚጠበቅበትንም ሚና በአግባቡ እንዲጫወት ለማስቻል ጥንዶችን ጨምሮ ባለድርሻ አካላት በቅንጅት እንዲሰሩ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጥሪውን ያቀርባል፡፡
