‎ስትራቴጂው የአሁኑንና የወደፊቱን ወጣቶች ሁለንተናዊ ስብዕና ለመቅረፅ በሚያስችል መልኩ እየተዘጋጀ ነው – ክብርት ሙና አህመድ

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከዲኤስ ደብሊው (DSW) የበጎ አድራጎት ድርጅት ጋር በመተባበር የኢትዮጽያ ወጣቶች ስብዕና ስትራቴጂ ረቂቅ ሰነድ ላይ የወይይትና ግብዓት የማሰባሰቢያ መድረክ አካሂዷል።

‎‎በመድረኩ ላይ የወጣቶች ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሙና አህመድ ስብዕናው የተገነባ ወጣት ከራስ ባለፈ ለማህበረሰብ ለውጥና ለሀገር ብልፅግና ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል። ‎የዛሬና የነገ ሀገር መሪዎች የሆኑት ወጣቶች ሁለንተናዊ ስብዕና ላይ መሰራት ቀዳሚ አጀንዳ መሆኑን በመገንዘብ ሚኒስቴሩ ስብዕና ልማት ላይ ያተኮሩ ተግባራትን በቅንጅት እያከናወነ መሆኑን ገልፀዋል። የወጣቶች ስብዕና ጉዳይ የተሻሻለው ብሔራዊ የወጣቶች ፖሊሲ ዋነኛ ማጠንጠኛ ምሰሶ ተደርጎ መቅረቡን እና ስትራቴጂውም ፖሊሲውን ለማስፈፀም ከተዘጋጁ ሰነድ መካከል አንዱ መሆኑን ተናግረዋል።

‎ስትራቴጂውን በዋነኝነት እያደገ ከመጣው የወጣቶች ቁጥርና ፍላጎት ባሻገር የሚስተዋሉ የወጣቶች ችግሮችን ደረጃ በደረጃ መፍታት እንዲሁም በተለያዩ ባለድርሻና አጋር አካላት በተበታተነ መልኩ የሚሰሩ ስራዎችን በተጀራጀ አግባብ መምራት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል።ስትራቴጂው የአሁኑንና የወደፊቱን ወጣቶች ሁለንተናዊ ስብዕና ለመቅረፅ በሚያስችል መልኩ መዘጋጁትንና ሰነዱን ለማዳበር የሚረዳ ግብዓት የማሰባሰብ ስራ እየተሰራ መሆኑን ክብርት ሙና አህመድ ተናግረዋል።

‎‎የዲኤስ ደብሊው (DSW) የበጎ አድራጎት ድርጅት ተወካይ ወ/ሮ በቀለች ባዩ በበኩላቸው፥ ድርጅቱ ላለፉት 25 አመታት በወጣቶች ላይ ያተኮሩ ተግባራትን ትስስር በመፍጠር ሲያከናውን መቆዩቱን ገልፀዋል። በመድረኩ ከተለያዩ የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅት የውጣጡ ተወካዮች፣ የወጣት ዘርፍ አመራሮችና ባለሙያዎች እንዲሁም የስትራቴጂ ጥናት ቡድን አባላት ተሳትፈዋል።

Please follow and like us: