Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከስዊዲን መንግስት ጋር በሴቶች ኢኮኖሚ ተጠቃሚነትና የማህበራዊ ጥበቃ ስርዐት ላይ በጋራ ለመስራት ተስማሙ።
የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ የስዊድን አምባሳደር ማግነስ ሌናርትሰን በትላንትናው ዕለት በፅ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

በውይይቱ ወቅት ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) እንደገለፁት ስዊድን በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ለሚገኙት የኢኮኖሚ ሪፎርሞች እያደረገች ላለችው አጋርነት አመስግነው ፣ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እና በስዊድን መንግስት መካከል ያለው ትብብር ለተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል። ሚኒስትሯ እንደገለፁት በሀገሪቱ ያለውን የማህበራዊ ጥበቃ ስርዐት ይበልጥ ለማዘመንና ዜጎችን ከጊዜያዊ ቀጥታ ድጋፍ በማውጣት በዘላቂነት በማቋቋም ለኢኮኖሚው የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ትኩረት በማድረግ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው በተጨማሪም የሴቶችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን በማሳደግና ወጣቶችን በስራ ፈጠራ ሂደት ይበልጥ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑም ሰፊ ስራ ዎች እየተከናወኑ እንዳሉ ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያ የስዊድን አምባሳደር ማግነስ ሌናርትሰን በበኩላቸው ስዊድን ለሴቶች ኢኮኖሚ ተጠቃሚነትና ማህበራዊ ጥበቃ ስርዐትን ዘላቂ በሆነ የኢኮኖሚ ትብብር ለማስቀጠል ቁርጠኛ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

በመጨረሻም ቀደም ሲል በዓለም አቀፍ የጉዲፈቻ ስርዓት ወደ ውጭ አገር የሄዱ ህፃናትን መረጃ ዲጂታላይዝ ለማድረግ እየተሰራ ያለውን ስራ በጋራ በመሆን ጎብኝተዋል። ኢትዮጵያና ስዊድን ለ75 ዓመታት የዘለቀ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዳላቸው ይታወቃል።
