Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ከኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጋር በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር ተስማሙ
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ከኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ዛሬ በፅቤታቸው ተቀብለው በማህበራዊ ልማት ስራዎችና በበጎ ፍቃድ አገልግሎት ዙሪያ ውይይት አድርገዋል።

በውይይቱ ወቅት ሚኒስትሯ እንደገለፁት የካቶሊክ ቤተክርስቲያን በኢትዮጵያ በተለይም ሴቶችን በተለያዩ የሙያ ስልጠናዎች እና የገቢ ማስገኛ ተግባራት በማብቃት፣ ለአረጋውያን፣ ለአካል ጉዳተኞች እና ውሎና አዳራቸውን በጎዳና ላይ ለሚኖሩ ወገኖች ማህበራዊ ተሃድሶና ድጋፍ በመስጠት፣ እንዲሁም ለችግር ተጋላጭ ለሆኑ ህፃናት በትምህርትና በእንክብካቤ አገልግሎቶች እያበረከተች ያለውን ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድንቀዋል። ሚኒስትሯ አክለውም የቤተክርስቲያኗ የበጎ አድራጎት ስራዎች ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎች ማህበራዊ ጥበቃን ለማረጋገጥ ከሚሰራው ስራ ጋር የተጣጣሙ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በመሆኑም ሁለቱ ወገኖች በተለይም በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ዙሪያ በጋራ ለመስራት እና የቤተክርስቲያኗን ሰፊ የበጎ ፈቃደኞች መረብ ለሀገራዊ የማህበራዊ ድጋፍ ዘመቻዎች ለማዋል ተስማምተዋል። ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ በበኩላቸው ቤተክርስቲያኗ “ሁለንተናዊ የሰው ልጅ እድገት” እንዲረጋገጥ ያላትን ቁርጠኝነት ገልጸው፣ በሀገሪቱ የበጎ አድራጎት እና የመረዳዳት ባህል እንዲጎለብት ከመንግስት ጋር በቅርበት መስራቷን እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።
